ቀጥታ፡

6ተኛው የሳዑዲ አረቢያ -ኢትዮጵያ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ተካሄደ

አዲስ አበባ፦ ግንቦት 14 / 2016 (ኢዜአ ):- 6ተኛው የሳዑዲ አረቢያ - ኢትዮጵያ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ   በሪያድ ከተማ ተካሄዷል፡፡

ከግንቦት 13-14  2016 ዓ.ም በተካሄደው   ስብሰባው ላይ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታየ አፅቀስላሴ የተመራ የልዑካን ቡድን ተሳትፎ አድርጓል።

ኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ና  በፓለቲካ፣ በፀጥታ፣ በኢንቨስትመንት፣ ንግድና ቱሪዝም መስኮች በትብብር ይሰራሉ።

በሁለቱ አገራት የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ላይም እነዚህን የበለጠ አጠናሮ ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር  ማድረጋቸው ተመልክቷል።


 

በስብሰባው መጨረሻ በሁለቱ ሀገራት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በእንስሳት ሀብት፣ በግብርና፣ በመሰረተ-ልማትና ኃይል፣ በማዕድን፣ በሰላምና ደህንነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል የስምምነት ቃለ ጉባኤ  መፈረሙም ተገልጿል።

ከጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ጎን ለጎንም  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ታየ አፅቀስላሴ   ከሳዑዲ አረቢያ የአካባቢ፣ የውሃና ግብርና ሚኒስትር ጋር ሁለቱ አገራት በተለይም በእንስሳት ሀብት ልማት ንግድ እና ኢንቨስትመንት ላይ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር  ማድረጋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም