ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙሃን ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል - አቶ እውነቱ አለነ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2016(ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙሃን ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን "የኢትዮጵያ ሚዲያ ለኢትዮጵያውያን ውጤታማ ሀገራዊ ምክክር" በሚል መሪ ሀሳብ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የስራ ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች ጋር ተወያይቷል።

በውይይቱ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር፣ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት ለመገንባት የተጀመረው ምክክር ውጤታማ እንዲሆን የመገናኛ ብዙሃን የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተመላክቷል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ፤ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች መግባባትን ለመፍጠር ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተለያዩ ስራዎችን በገለልተኛነትና በነጻነት ማከናወኑን ተናግዋል።

በዚህም ለምክክሩ ሂደት መሰረታዊ የሚባሉ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰው ሂደቱ ህዝቡ ዘንድ ተደራሽ እንዲሆን የመገናኛ ብዙሃን ውጤታማ ስራ ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የመገናኛ ብዙሃን የላቀ ሚና ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ጠቁመዋል።


 

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር፤ ኢትዮጵያ ችግሮቿን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁን በተከናወኑ ተግባራት በ10 ክልሎች እና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊ ልየታ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱን ከግንቦት 21 ጀምሮ በአዲስ አበባ ማካሄድ እንደሚጀምርና በቀጣይም ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንደሚቀጥል ገልጸዋል።


 

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ በበኩላቸው የምክክሩ ዋና ዓላማ ሀገራዊ መግባባትን መፍጠር ነው ብለዋል።

በህዝብና በመንግስት መካከል እንዲሁም በህዝብ እና በህዝብ መካከል መተማመን ማስረጽም ሌላኛው የምክክሩ ዓላማ መሆኑን አንስተዋል።

በውይይቱ የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ እና ጋዜጠኛ ወንደወሰን ሽመልስ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የሚዲያው ሚና እና አበርክቶ በሚል መሪ ሃሳብ ጽሁፍ አቅርበዋል።


 

የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ መገናኛ ብዙሃን የምክክሩን መሰረታዊ ጉዳይ ለህዝቡ ተደራሽ በማድረግ ረገድ ተሳትፏቸው እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

መገናኛ ብዙሃን በዜና፣ በፕሮግራም እና በሌሎች ዝግጅቶች መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ረገድ የበለጠ መስራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።


 

ጋዜጠኛ ወንደወሰን ሽመልስ መገናኛ ብዙሃን ሀገራዊ ምክክሩን በተመለከተ የሚሰሯቸው ስራዎች የበለጠ እንዲጠናከሩ የሚዲያ ፎረም ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ እየመከረች መሆኑን በግልጽ በማስረዳትና ህዝቡ በምክክሩ በንቃት እንዲሳተፍ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በወይይቱ የተሳተፉ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የስራ ሀላፊዎች የምክክሩ ሂደት ውጤታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።


 

የአሃዱ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት ስራ አስፈጻሚ እና የሚዲያ ፎረሙ ምክትል ሰብሳቢ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ መግባባትና አንድነት እንዲፈጠር ለመስራት የፎረሙ አባል መገናኛ ብዙሃን መግባባት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ጌትነት ታደሠ በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃን አቅሞቻችንን በማስተባበር ለምክክሩ ስኬት በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።


 

የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን በዳሳ ተቋማቸው መረጃዎችን ተደራሽ በሚያደርግባቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ቋንቋዎች ሰፋፊ ዘገባዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ከሌሎች መገናኛ ብዙሃን ጋር በመቀናጀት ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም