በገጠራማ አካባቢዎች የታዳሽ ኃይል አማራጮችን በመጠቀም የኃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በገጠራማ አካባቢዎች የታዳሽ ኃይል አማራጮችን በመጠቀም የኃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2016 (ኢዜአ)፦ በሀገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች የታዳሽ ኃይል አማራጮችን በመጠቀም የኃይል አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
ለሁለት ቀናት የሚቆየው 2ኛው ዓለም አቀፍ የደቡብ-ደቡብ ትብብር ጉባዔ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።
የሀገራትና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች የተሳተፉበት ጉባዔም ያልተማከለ የታዳሽ ኃይል አጠቃቀም፣ ዘላቂ ልማት፣ ፈጠራና እውቀትን በመጋራት ዓለም አቀፍ ትብብር ለማጎልበት ያለመ ነው።
በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ የኢነርጂ አማካሪ ጎሳዬ መንግሥቴ፤ ኢትዮጵያ በውሃ፣ ጸኃይ፣ ነፋስና እንፋሎት የታዳሽ ኃይል አማራጮች ከፍተኛ የመልማት ጸጋ ያላት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
የታዳሽ ኃይል ልማት ለአስተማማኝ የኢኮኖሚ ግንባታና በትብብር የተመሰረተ ቀጣናዊ የልማት ትስስርን ለመፍጠር ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።
የታዳሽ ኃይል መሰረተ ልማት አቅርቦት የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁሉ አቀፍ ምርታማነትን ለማሳደግ በፍጥነት ለምቶ ጥቅም ላይ መዋል እንዳለበትም ተናግረዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ኢነርጂ የሁለንተናዊ ኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት መሆኑን በመገንዘብ የኃይል አቅርቦት ባልተዳረሰባቸው የገጠራማ አካባቢዎችን ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለታዳሽ ኃይል ልማት የሰጠው ትኩረትም በግብርና ምርታማነት፣ በአየር ንብረት ለውጥና ድህነት ቅነሳ ላይ ስኬት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት የሰፋፊ የልማት ጸጋና አቅም ባለቤት በመሆናቸው በትብብር ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ ግንባታን ማሳለጥ እንደሚጠበቅም አንስተዋል።
የደቡብ ደቡብ ትብብርም የዕውቀትና ልምድ ልውውጥ በመፍጠር የቴክኖሎጂና ኃይል ልማት መፍጠር የሚያስችል በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ልማትን ለማሳለጥ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
በመድረኩ የተሳተፉት የፕሪሳይስ አማካሪ ደርጅት ሥራ አስኪያጅ ሔኖክ አሰፋ፤ በታዳሽ ኃይል የተመሰረተ አስተማማኝ ኢኮኖሚ መገንባት የደቡብ ደቡብ ትብብር ጉባኤ ዋነኛ ዓላማ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ፣ እስያ፣ ላቲን አሜሪካ ሀገራት የሚፈጠሩ የዘርፉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችም ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና እንዲኖራቸው ለማስቻል የልምድና ተሞክሮ ልውውጥ ለማድረግ እንደሚረዳ ገልጸዋል።
በታዳሽ ኃይል የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎች ይበልጥ በማስፋት በተለይም በግብርና ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን መጨመር የሚያስችሉ ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ዓለም አቀፍ አጋሮች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ቴክኖሎጂና ሥራ ፈጣሪዎች፣ ባለሃብቶች፣ ምሁራን ጨምሮ ከ500 በላይ አካላት በተሳተፉበት ጉባኤ የታዳሽ ኃይል ፈጠራ ግኝቶቻቸውን የሚያሳዩበት ኤግዚቢሽንም ተዘጋጅቷል።
የመጀመሪያው የደቡብ ለደቡብ የትብብር ጉባኤ ከሁለት ዓመት በፊት በሕንድ መካሄዱ ይታወሳል።