ቀጥታ፡

የቦንጋ ቡና ጥራት ምርመራና ሰርቲፊኬሽን ማዕከል ተመርቆ ለአገልግሎት በቃ

ቦንጋ ፤ግንቦት 14/2016 (ኢዜአ)፦የቡና ጥራትን ለማስጠበቅ የተገነባው የቦንጋ ቡና ጥራት ምርመራና ሰርቲፊኬሽን ማዕከል ተመርቆ ለአገልግሎት በቃ።

ማዕከሉን መርቀው ሥራ ያስጀመሩት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዞቦች ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ እና የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ናቸው።

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ቡና ለክልሉ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆኑ የምርት ጥራትን በመጠበቅ የዘርፉን ገቢ ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ ነው።

በዚህም የተሻለ ለውጥ መታየቱን የገለጹት ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ፣ ባለፉት ወራትም ከክልሉ 44 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ጠቅሰዋል።


 

የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ለማሳካት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀው፣ የቡና አመራረት እና የማጓጓዣ ሥርአቱን ማሻሻል እንደሚገባ አሳስበዋል። 

በቦንጋ ከተማ ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው ማዕከል ክልሉ በቡና ምርት ካለው ዕምቅ አቅም አኳያ ለሚዛን አማንና ቴፒም ተጨማሪ አገልግሎት መስጠት እንዳለበትም አመልክተዋል።

የቦንጋ የቡና ምርት ጥራት ምርመራና ሰርተፊኬሽን ማዕከል እንዲከፈት ትብብርና ዕገዛ ያደረጉ አካላትን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አመስግነዋል።

ማዕከሉ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ስለሚያደርግ ህብረተሰቡ ሊጠብቅውና ሊንከባከበው እንደሚገባ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ ባለስልጣኑ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱን በመፈተሽ አሰራሩን እያሻሻለ ይገኛል። 


 

ዛሬ ለአገልግሎት የበቃው ማዕከል የቡና ጥራት ደረጃን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያረጋግጥ ገልጸዋል።

"በቀጣይም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ተጨማሪ ማዕከላትን ለመክፈት ከክልሉ ጋር በመተባበር  ይሰራል" ሲሉም ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።

በሀገር ደረጃ በዓመት 300ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ለመላክ የሚያስችል አቅም መፈጠሩን ዶክተር አዱኛ ጠቁመው፣ "ለጥራት ትኩረት በመስጠት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ማሳደግ ይገባል" ብለዋል።  

በኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ኡመር በበኩላቸው፤  ባለስልጣኑ የቡና ልማትና ግብይት ላይ ከፍተኛ ለውጥ በመፍጠር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

ከዚህ ቀደም ቡና ላይ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት በተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች አማካኝነት በየዓመቱ ከቡና የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል።

ባለፉት አስር ወራት ብቻ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል ሲሉ ነው ገለጹት።

በቡና ልማት የሀገርን እና የአርሶ-አደሮችን ተጠቀሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት መደረጉን የገለፁት አቶ ሻፊ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ብቻ ተወስነው የነበሩ የቡና ምርመራና ሰርትፊኬሽን ማዕከላት መላ ሃገሪቱን በሚያማክል ሁኔታ እየተስፋፉ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ቡና ከኢኮኖሚ ጠቀሜታው ባለፈ የካፋ ህዝብ የታሪክ አካል መሆኑን የገለፁት ደግሞ የካፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ደምመላሽ ንጉሴ ናቸው።


 

ዛሬ የተመረቀው ማዕከል የህዝብ የልማት ጥያቄን መፍታቱን ጠቁመው፣ ማዕከሉ ቡናን በጥራትና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ምቹ መደላድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

ማዕከሉ በቦንጋ ከተማ እንዲቋቋም አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ከክልሉ መንግስት እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም