በቀጣይ ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ አስቀድመው ለተዘሩ ለበልግ ሰብሎች አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
በቀጣይ ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ አስቀድመው ለተዘሩ ለበልግ ሰብሎች አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2016(ኢዜአ)፦ በቀጣይ ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ አስቀድመው ለተዘሩ የበልግ ሰብሎች፣ ለቋሚ ተክሎችና ለጓሮ አትክልቶች የውሃ ፍላጎትን ከማሟላት አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ።
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በቀጣይ ዘጠኝ ቀናት በመጠንና በሥርጭት የተስፋፋ ዝናብ ይኖራል ብሏል።
በዚህም በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብና ሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው ተመላክቷል።
የአየር ሁኔታው አስቀድመው ለተዘሩ የበልግ ሰብሎች፣ ለቋሚ ተክሎችና ለጓሮ አትክልቶች የውሃ ፍላጎትን ከማሟላት አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋልም ተብሏል።
ከቀጣይ ግንቦት 24 ጀምሮ አስቀድመው ለሚዘሩ የመኸር ሰብሎች የማሳ ዝግጅት ለማከናወንና ዘር ለመዝራት አዎንታዊ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑም በመግለጫው ተጠቅሷል።
በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች የረጅም ጊዜ ሰብሎችን ለመዝራትና ለቋሚ ተክሎች እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ለተተከሉ የዛፍ ችግኞች እድገት የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ተጠቅሷል።
የሚገኘው እርጥበት በአርብቶ አደርና በከፊል የአርብቶ አደር አካባቢዎች የእጽዋት ልምላሜን የግጦሽ ሳርንና የመጠጥ የውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል ጠቀሜታ እንዳለውም ተገልጿል።
የሚጠበቀው ከፍተኛ እርጥበት በተለይም በረባዳማ ቦታዎች የሚገኙ የሰብል ማሳዎች ላይ የእርጥበት መብዛት እና ውሃ በሰብሎች ላይ መተኛት እንዳያስከትል የውሃ ማንጣፈፍ እንዲሁም የጎርፍ መቀልበሻ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም ተጠቅሷል።
በመካከለኛውና ታችኛው ተከዜ፣ አባይ፣ ባሮ አኮቦ፣ ኦሞ ግቤ፣ የላይኛውና የመካከለኛው አዋሽ፣ የስምጥ ሸለቆ የላይኛው ዋቤ ሸበሌና የገናሌዳዋ ተፋሰሶች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከከፍተኛ መጠን ያለው እርጥበት ይጠበቃልም ተብሏል።
ይህም ሁኔታ ተፋሰሶች የተሻለ የውሃ መጠን እንዲኖራቸው ከማድረግ አንጻር አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረውና ለመስኖና ለሃይል ማመንጫነት የሚያገለግሉ የግድቦችን የውሃ መጠን እንደሚያሻሽልም ተጠቁሟል።
ከባለፉት ወራት ጀምሮ በተለያዩ ተፋሰሶች ላይ ከፍተኛ የእርጥበት መጠን የተስተዋለ በመሆኑ በጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅትና ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው በመግለጫው የተብራራው።