ቀጥታ፡

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው  መቀጠል አለባቸው - ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2016(ኢዜአ)፦  ከወጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተከናወኑ ያሉ  ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳስቧል።

በምክር ቤቱ የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ገምግሟል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የተቋሙን የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም አቅርበዋል።

በዚህም የክትትልና ግምገማ ስርዓት መዘርጋት፣ የሰው ሃብት አስተዳደር፣ መረጃን በቴክኖሎጂ ከመደገፍ አኳያ፣  የአምራች ኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦት፣ የአምራች ኢንዱስትሪ የወጪ ተኪ ምርት መጠን ከማሻሻል እና ኢንቨስትመንት ከመሳብ አኳያ የተሰሩ ስራዎችን አንስተዋል።


 

የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ለማሳደግ የግብዓት አቅርቦትን የማሻሻል፣ የፋይናንስና የሃይል አቅርቦትን ከማሳደግ ፣ እንዲሁም ከሰው ኃይል አቅርቦት አንጻር ተስፋ ሰጪ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።

የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም እንዲጨምር በተሰሩ ስራዎች ሀገራዊ የኢንዱስትሪ የማምረት አቅም ከ56 በመቶ በላይ መድረሱን ተናግረዋል።

የተኪ ምርቶች ስትራቴጂ በተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ገልጸው በዚህም የጸጥታ አካላት የደንብ ልብስ ፣የቢራ ብቅልን ጨምሮ ሌሎች ምርቶችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉን ተናግረዋል።

እንዲሁም በተኪ ምርት 3 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ግምት ያላቸው 2 ነጥብ 2 ሜትሪክ ቶን ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካቱንና 1 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማዳን መቻሉን ጠቅሰዋል።


 

የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር አማረች ባካሎ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች እየተፈጠረ ያለው የግብዓት፣ የገበያ ትስስር፣ የብድር እና የሃይል አቅርቦት ከበጀት አመቱ የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈፃፀም አኳያ የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል።

ከኢንዱስትሪዎች ሽግግር አኳያም ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ የሚደረገው ሽግግር ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸው ፤ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ በሚደረግ ሽግግር ላይ ተጨማሪ ስራዎችን በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ኬሚካልና ኮንስትራክሽን እንዲሁም በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት የተሻለ ነው ብለዋል።

ከተኪ ምርት አፈፃፀም አንፃር የተከናወኑ ተግባራት ከበጀት አመቱ የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈፃፀም አኳያ የሚበረታቱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የአገር ውስጥ የገበያ ድርሻን ከማሳደግ አንፃር የተከናወኑ ሥራዎች አፈፃፀም ከበጀት አመቱ የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈፃፀም አኳያ የተሻለ መሆኑን አንስተው በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተጀመሩ ስራዎች  አበረታች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሰለጠነ የሰው ሃይል አቅርቦትን ከማሻሻል አኳያ የሚከናወኑ ስራዎች ትኩረት የሚሹ እንደሆነ አንስተዋል።

አምራች ኢንዱስትሪዎች እና ኢንተርፕራይዞች የመረጃ ቋት እንዲኖራቸው ለማድረግ መስራት እንደሚገባም ተመላክቷል።

አዳዲስ ምርቶችን ለውጪ ገበያ ለማቅረብ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም