በአረንጓዴ ልማት የተፈጥሮ ጥበቃና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የብዝሃ ህይወት ጥበቃ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአረንጓዴ ልማት የተፈጥሮ ጥበቃና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የብዝሃ ህይወት ጥበቃ ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2016(ኢዜአ)፦ በአረንጓዴ ልማት የተፈጥሮ ጥበቃና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የብዝሃ ህይወት ጥበቃ ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዓለም አቀፍ የብዝኃ ሕይወት ቀንን በማስመልከት ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፈለቀ ወልደየስ (ዶ/ር)፤ የሰው ልጆች የእለት የኑሮ ሁኔታ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከብዝሀ ሕይወት ጋር የተቆራኘ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለሰው ልጆች መሠረታዊ ፍላጎት መሟላት፣ ለተፈጥሮና አካባቢያዊ ምቹነት የብዝኃ ሕይወት አስተዋጽዖ ከፍተኛ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
በመሆኑም የብዝሀ ሕይወት ልማትና ጥበቃ ኢንስቲትዩት የአገራት ተሞክሮ በመቀመር በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ በስፋት እየተከናወነ ላለው የአረንጓዴ ልማትና የምግብ ዋስትና መርሃ-ግብር መሳካት የብዝሀ ሕይወት ጥበቃ ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ የብዝሀ ሕይወት ልማትና ጥበቃ ኢንስቲትዩት እያደረገ ያለው ጥረት እንዳለ ሆኖ የሁሉም ባለድርሻ አካላትና የዜጎች ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በኢንስቲትዩቱ የደንና ግጦሽ መሬት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አበራ ስዩም፤ ከብዝሀ ሕይወት የሚገኙ ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞችን ማስፋትና ዘለቄታዊ ጥቅሞችን ማስረጽ ላይ የጋራ ሥራ ያስፈልጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በብዝሀ ሕይወት ሃብታም ከሚባሉት አገራት መካከል መሆኗን ጠቅሰው፤ እስካሁን አምስት የተፈጥሮ ኃብቶች በዓለም ቅርስነት መመዝገባቸውን አስታውሰዋል።
በቅርቡም ተጨማሪ አንድ የብዝሀ ኃብት ተፈጥሮን ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አክለዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ ግርማ እሸቱ (ዶ/ር) ፤ የጥብቅ ደኖች ደኅንነትና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለማጉላት የተዘጋጀውን ረቂቅ ፖሊሲ በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል።
የፖሊሲውን ይዘትና አስፈላጊነት ለባለድርሻ አካላት የማስገንዘብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
እስካሁን የጥብቅ ደኖች ደኅንነትን ለማስጠበቅና የአጠቃቀም ሥርዓትን ማረጋገጥ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩን አስታውሰው፤ የፖሊሲን አስፈላጊነት አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ''የዕቅዱ አካል እንሁን'' በሚል መሪ ሃሳብ ዓለም አቀፍ የብዝሀ ሕይወት ቀንን ምክንያት በማድረግ ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የቆየው መርሃ-ግብር ዛሬ ተጠናቋል።