ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ ዲጅታል መር ኢኮኖሚ ለመገንባት በምታደርገው ጥረት የግሉ ዘርፍ የመሪነት ሚና መጫወት አለበት-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ ዲጅታል መር ኢኮኖሚ ለመገንባት በምታደርገው ጥረት የግሉ ዘርፍ የመሪነት ሚና መጫወት አለበት-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በ2025 በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ ዲጅታል መር ኢኮኖሚ ለመገንባት በምታደርገው ጥረት የግሉ ዘርፍ የመሪነት ሚና መጫወት እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።
መንግስት የዲጅታል ስትራቴጂ ትግበራን ለማፋጠን የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱንም ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ሚኒስትሮችና የቴክኖሎጂ ዘርፍ ባለድርሻዎች በተገኙበት ከስትራይድ ኢትዮጵያ ኤክስፖ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽን አይቀሬ በመሆኑ ወሳኝ ኢኒሼቲቮችን ቀርፃ መተግበር ጀምራለች ብለዋል።
ለኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግርን ማረጋገጥ የግድ የሆነባቸው ምክንያቶች አሉ ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዲጂታላይዜሽን ዕድገትን ማፋጠን ዋነኛው መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል መንግሥታዊ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እንዲሁም ለማህበራዊ ፍትሐዊ ተደራሽነትም ጉልህ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን አንስተዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ መገንባት የሚያስችል እምቅ ፀጋ አላት ብለዋል።
በፖሊሲ ደረጃ በአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ አይ ሲ ቲ ከአምስቱ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ ሆኖ እየተሠራበት እንደሚገኝና በመሠረተ-ልማትም በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በ2025 ከአፍሪካ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ግንባር ቀደም ተጠቃሚ ሀገር እንድትሆን የተቀመጠውን ትልም ለማሳካት መንግስት ትላልቅ ኢኒሼቲቮችን እየተገበረ ነው ብለዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑንም ለአብነት አንስተዋል።
በአንጻሩም የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን ከዲጅታላይዜኝን ጋር በተናበበ መልኩ ለመተግበር በሙከራ ደረጃ መጀመሩን ገልጸዋል።
መንግሥት ለዘርፉ እውን መሆን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት አቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱንም ተናግረዋል።
የመጀመሪያው ዓላማ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማሳደግ ከመንግስት ጋር ቅንጅታዊ አሠራርን ለማጠናከር መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላኛው ዓላማ በመንግስት ተቋማት ወጪ ቆጣቢ አሠራር እንዲተገበር ለማድረግ መሆኑንም አንስተዋል።
መንግስት ዲጅታላይዜሽንን በማፋጠን ረገድ የግሉ ዘርፍ የመሪነት ሚና እንዲወጣ የሚያደርግ የዕይታ ለውጥ እየተከተለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች፣ የምርምር ተቋማትና ባለሀብቶች ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን የዲጅታል ኢኮኖሚ ለመገንባት በቅንጅት እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ስትራይድ ኢትዮጵያ ኤክስፖ "ሳይንስ በር ይከፍታል፤ ቴክኖሎጂ ያስተሳስራል፤ ፈጠራ ወደፊት ያራምዳል" በሚል መሪ ኃሳብ በሳይንስ ሙዚየም እስከ ግንቦት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ለሕዝብ ዕይታ ክፍት ሆኖ ይቆያል።