በተያዘው አመት ለ 700 የአዝዕርትና ሆርቲካልቸር ናሙናዎች ጥበቃ ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በተያዘው አመት ለ 700 የአዝዕርትና ሆርቲካልቸር ናሙናዎች ጥበቃ ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2016(ኢዜአ)፦ በተያዘው አመት ለ 700 የአዝዕርትና ሆርቲካልቸር ናሙናዎች ጥበቃ መደረጉን የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት ገለፀ።
በኢንስቲትዩቱ የአዝዕርትና ሆርቲካልቸር ምርምር መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ውብሸት ተሾመ ለኢዜአ እንዳሉት በብዝሀ ህይወት ጥበቃ የማንበር፣ ከአካባቢያቸው የጠፉ ዝርያዎችን መልሶ የመተካትና አሳታፊ የነባር ዘር ምርምር በመሰራት ላይ ይገኛል።
ባለፉት 48 አመታት ከ91 ሺህ በላይ የአዝዕርትና ሆርቲካልቸር ናሙናዎች የመጠበቅና ከአካባቢያቸው የጠፉ 18 አይነት የሰብል ዝርያዎችን በማባዛት መልሶ መተካት መቻሉን ነው ያስረዱት።
በተያዘው አመት በአዝዕርትና ሆርቲካልቸር ዘርፍ በእያንዳንዳቸው 350 በድምሩ የ 700 ናሙናዎች ጥበቃ መደረጉን ጠቅሰው በአራት አይነት ሰብሎች ላይ አርሶ አደሩን ያሳተፈ የምርምር ስራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
በቀጣይም በአርሶ አደሮች እጅ የሚገኙ ዝርያዎችን ናሙና በመሰብሰብ በማቀዝቀዣ ክፍልና በመስክ ጅን ባንክ የማንበር ስራ እንደሚሰራ ነው የጠቆሙት።
በኢንስቲትዩቱ የእንስሳት ብዝሀ ህይወት ምርምር መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ተስፉ ፈከንሳ በበኩላቸው የአገሪቱን የእንስሳት ብዝሀ ህይወት የመለየትና አደጋ የተጋረጠባቸውን ቅድሚያ በመስጠት በመስክና በጂን ባንክ የማንበር ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ዝርያቸው መመናመኑ ከተለዩ አምስት የፎገራ፣ የሸኮ፣ የቦረና፣ የቤጋይትና የሂሮብ የዳልጋ ከብት ዝርያዎች የወንድ አባላዘር በመሰብሰብ በጂን ባንክ ጥበቃ ተደርጓል ብለዋል።
የወንድ አባላዘር መልሶ በማሰራጨት የተመናመኑ ዝርያዎችን ቁጥር ለማበራከት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ለአብነትም 3 ሺህ 500 የነበረው የሸኮ ዳልጋ ከብት ዝርያ ወደ 8 ሺህ ከፍ ማለቱን አንስተዋል።
አብዛኛው የምንበላቸው ምግቦች በነፍሳት ላይ ጥገኛ ናቸው ያሉት ዶክተር ተስፉ የነፍሳት ቁጥርም እየተመናመነ በመምጣቱ መልሶ ለመተካት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ንብ ማነብ ለዚህ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን ጠቅሰው ኢንስቲትዩቱ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር መነሻነት በስምንት ማዕከላት ዘመናዊ የንብ ቀፎ በማሰራጨት ሞዴል ማዕከል እንዲሆኑ እየሰራ ነው ብለዋል።