ቀጥታ፡

የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ተግባራዊ እንዲሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየተሰራ ነው - የአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2016(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ተግባራዊነት እንዲፋጠን ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር ዋና ጸሃፊ አብዱራሃማን በርቴ ገለጹ።

ኢትዮጵያን ጨምሮ 17 የአፍሪካ ሀገሮች የአህጉሪቱን አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ገበያ በሙከራ ደረጃ ለመጀመር መስማማታቸው ይታወሳል።

ስምምነቱ ንብረትነታቸው ሙሉ ለሙሉ አፍሪካዊ የሆኑ አየር መንገዶች ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው በሚያደርጉት የንግድና ገበያ ተኮር በረራ የተጣሉ ገደቦችን የሚያስቀር ነው።

የአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር ዋና ጸሃፊ አብዱራሃማን በርቴ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የአፍሪካ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ በሚጠበቀው ልክ እንዳያድግ የሚገድቡ ዘርፈ ብዙ ማነቆዎች ይስተዋላሉ።

ከእነዚህ መካከል በአህጉሪቱ በቂ የአየር ትራንስፖርት አለመኖርና የዋጋ ንረት፣ ከጥቂት አየር መንገዶች በስተቀር ምቹና ደህንነታቸው የተጠበቀ አየር መንገዶች አለመኖራቸው ይጠቀሳል።

የዘርፉን ተግዳሮት ለመቅረፍ እንዲሁም በአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ገበያን ለማፋጠን ፖሊሲ አውጪዎች በትኩረት ሊሰሩ የሚገባበት ወቅት ላይ እንገኛለን ሲሉም ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ተግባራዊ መሆን ለአቬዬሽን መስኩ እድገትና የእርስ በእርስ የገበያ ትስስርን ለማስፋት የላቀ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ብዙ ሀገራት ስምምነቱን መፈረማቸው በበጎ የሚነሳ መሆኑን የገለጹት የማህበሩ ዋና ጸሃፊ፣ ነገር ግን ተግባራዊ ማድረግ ላይ ፈጣን እርምጃ አለመወሰዱን ጠቁመዋል።

ይህንን ለማፋጠንም የአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በተለይም የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን ጉዳዩን በዋናነት ይዞ እየሰራ መሆኑን በመጠቆም።

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ተግባራዊ መሆን ሲጀምር የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ለአህጉሪቱ ገበያ መስፋፋት የላቀ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።

በመሆኑም፣ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ያሉትን የገበያ አማራጮች ለመጠቀምና ለአየር ትራንስፖርት እድገት በጋራ መስራት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም