በደሴ ከተማ ገበያውን ለማረጋጋት የተደረገው ጥረት ውጤት እያመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደሴ ከተማ ገበያውን ለማረጋጋት የተደረገው ጥረት ውጤት እያመጣ ነው

ደሴ፤ ግንቦት 14 ቀን 2016(ኢዜአ)፡-በደሴ ከተማ የምርት አቅርቦት እጥረት ችግርን በማቃለል ገበያን ለማረጋጋት የተደረገው ጥረት ውጤት እያመጣ መሆኑን የከተማው አስተዳደር ኅብረት ስራ ማህበር ማስፋፊያ ተጠሪ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
"የኅብረት ሥራ ሪፎርም ከማደራጀት ባሻገር" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የኅብረት ስራ ሪፎርም ንቅናቄ መድረክ በደሴ ተካሂዷል፡፡
የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ ተስፋዬ እንደገለጹት፤ ጽህፈት ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ገበያውን የማረጋጋት ስራ እያከናወነ ይገኛል፡፡
በዚህም ምርት ካለበት አካባቢ በማስመጣት የአቅርቦትና ፍላጎት ክፍተቱን በማስተካከል የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ በተደረገው ጥረት ውጤት እያመጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸው 20 ሚሊዮን ብር በተጨማሪ በዩኔዮኖችና በኅብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ምርት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የዋጋ ጭማሪውን ማረጋጋት ተችሏል ብለዋል፡፡
በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች በ3 ወር በሚከፍል ዱቤ ጭምር መሰጠቱ ለዜጎች እፎይታ መፍጠሩንም አመልክተዋል፡፡
በደሴ ከተማ የሚገኘው የላኮመልዛ ሸማቾች ዩኔን ሥራ አስኪያጅ አቶ የሱፍ መሃመድ በበኩላቸው፤ በከተማው ገበያን ለማረጋጋት የተጀመረው ቅንጅታዊ ስራ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸውና በዩኔየኑ ገንዘብ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ17 ሺህ ኩንታል በላይ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረብ መቻሉን አስረድተዋል።
ምርት ካለበት አካባቢ ወደ ከተማው በማስመጣት የምርት እጥረት እንዳይከሰት መደረጉ ከስግብግብ ነጋዴዎች የዋጋ ጭማሪ መከላከል እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡
ከ60 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ገንዘብ ምርት በማቅረብ የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ ጥረቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡
በከተማው በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ ካለው የተለያየ ምርት በተጨማሪ በ3 ወር የሚከፈል በዱቤ ጭምር ምርት ማግኘታችን እፎይታን ፈጥሮልናል የሉት ደግሞ የደሴ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አለም ተክለማሪያም ናቸው፡፡
ጤፍና የዳቦ ዱቄት ጨምሮ ሌሎችም የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች እንደቀረቡላቸውም ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት፣ የአስተዳደሩና የሸማች ማኅበራት የአመራር አባላት እንዲሁም የዘርፉ ባለሙያዎችና ሌሎችም አካላት ተሳትፈዋል።