የአፍሪካ ዓለም አቀፍ የቅርሶች ቀን በጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ ነገ ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ዓለም አቀፍ የቅርሶች ቀን በጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ ነገ ይከበራል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የአፍሪካ ዓለም አቀፍ የቅርሶች ቀን ነገ በጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ እንደሚከበር አስታወቀ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት ፤ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) እ.ኤ.አ በኅዳር 2015 ባካሄደው 38ኛው ጉባዔ ግንቦት 5 ቀን የአፍሪካ የዓለም ቅርስ ቀን እንዲሆን ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በዚሁ መሠረት ቀኑ በአህጉር ደረጃ ለስምንተኛ በሀገራችን ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ነገ ግንቦት 15 ቀን 2016 ዓ.ም "ትምህርት ለአፍሪካ አለም ዓቀፍ ቅርሶች ጥበቃ" በሚል መሪ ሃሳብ በጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ ይከበራል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ለኢዜአ በላከው መግለጫ ፤ቅርሶቻችን የአባቶቻችን የፈጠራ መዘከር ማኅተም ያረፈባቸውና የኅብረ ብሄራዊ አንድነታችን ጥንካሬና ጉልበት መገለጫ ናቸዉ ብሏል ፡፡
በአገራችን የባህል እና የተፈጥሮ ቅርሶች መልማት እና መጠበቅ ከመስህብነት በዘለለ ለመልካም ገጽታ ግንባታ እና ለምጣኔ ሀብት እድገት ያላቸውን ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
የቀኑ መከበር በቅርስ ዙሪያ የወጡ ዓለም አቀፍ አዋጆችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን በተመለከተ ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ለመፍጠር ያግዛል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም የቱሪዝም ፍሰት እንዲጨምር ፣ቅርሶች ለአንድ ሀገር ዕድገት ያላቸውን ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ የሚረዳ ትውልድ ወይም ማህበረሰብ እንዲኖር ያግዛል፡፡
ከዚህ ባለፈ ቅርስ መጠበቅ የሁለም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ግንዛቤ ለመፍጠር የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት በመግለጫው ተጠቅሷል ፡፡
ቀኑ በባህላዊ እና በተፈጥሮ የመስህብ በረከቶች አጠባበቅ ሂደት ላይ በሚታዩ ተግዳሮቶች ዙሪያ በመምከር የመፍትሄ ሀሳቦችን ለማቅረብ እንደሚያግዝም እንዲሁ ፡፡
የሀገሪቱን ባህላዊ ፣ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ ቅርሶች ሁለንተናዊ እሴታቸውን ከስጋት እና ጉዳት በመከላከል እና በመጠበቅ ለማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማዋል ይረዳል፡፡
በዚህም ሃብቶቹን ለሚቀጥለዉ ትውልድ ለማስተላለፍ የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ትብብር ለማገዝ እድል እንደሚፈጥር ተገልጿል፡፡
እ.ኤ.አ በ1978 ዩኔስኮ ለመጀመሪያ ጊዜ የላቀ ሁለንተናዊ እሴትነት ያላቸውን ቅርሶች በመለየት ከመዘገባቸው 12 ቅርሶች መካከል ከአህጉሪቱ የተመረጡት ሦስት ቅርሶች ሲሆኑ ከነዚህ ሀገራችን ሁለቱን በማስመዝገብ በአፍሪካ የቀዳሚነቱን ቦታ ወስዳለች፡፡
በአሁኑ ጊዜም ከ 46 የአፍሪካ አገራት የተመረጡ 147 ቅርሶች በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ሲሆን ከነዚህ መካከል ኢትዮጵያ 11 ቅርሶችን በማስመዝገብ በክፍለ አህጉሩ የመሪነቱን ሚና መያዟን መግለጫው አመላክቷል፡፡