ቀጥታ፡

ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል- ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት

አርባ ምንጭ ፤ ግንቦት 14/2016(ኢዜአ)፡- ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ከህብረተሰቡ ድጋፍ መደረጉን የሕዳሴው ግድብ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

"በህብረት ችለናል" በሚል መሪ ሀሳብ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የድጋፍ ንቅናቄ መድረክ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተካሄዷል።


 

ዩኒቨርሲቲው ከፌዴራል፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልልና ከጋሞ ዞን ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቶች ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በእዚህ መድረክ ላይ ግድቡን የተመለከተ ሰነድና የተለያዩ የስነ-ጽሑፍ ሥራዎች ለታዳሚው ቀርቧል።

በዚህን ወቅት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር ለኢዜአ እንዳሉት ህብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገው ድጋፍ በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥሏል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ገቢ ለመሰብሰብ በተደረገ እንቅስቃሴም ለግድቡ ግንባታ ከ1 ቢሊዮን 140 ሚሊዮን ብር በላይ ከህብረተሰቡ ለመሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።

ህዝቡ በገንዘቡ፣ በዕውቀቱ፣ በጉልበቱ፣ በዓይነት እና በሞራል የሚያደርገውን ድጋፍ እያጠናከረ መሆኑንም አንስተዋል።

የግድቡ ግንባታ በአሁኑ ወቅት 96 በመቶ መድረሱና በተወሰነ ደረጃ ሃይል የማመንጨት ሥራ መጀመሩንም ወይዘሮ ፍቅርተ አስታውቀዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በርካታ የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን አልፎ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ መድረሱን አስታውሰው፣ ግድቡ ኢትዮጵያዊያን ከተባበርን ፈተናዎችን ተቋቁመን ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደምንችል ያሳያል ብለዋል። 

ግድቡ ተባብረን ከሰራን የሀገሪቱን ብልጽግና ማረጋገጥ እንደምንችል ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በተግባር ያስመሰከርንበት ፕሮጀክት ጭምር ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን በሁሉም የሙያ ዘርፍ  እያደረጉት ላለው ድጋፍ ያመሰገኑት ወይዘሮ ፍቅርተ፣ ቀሪ የግንባታ ሥራዎች እንዲጠናቀቁም የህብረተሰቡ ድጋፍ መጠናከር አለበት ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሚልኪያስ እስራኤል በበኩላቸው ግድቡ የኢትዮጵያን የሕዳሴ ጉዞ ከማሳለጥ አኳያ ፋይዳው የጎላ መሆኑን  ነው የተናገሩት።

"ኢትዮጵያዊያንን አንድ ያደረገና የይቻላል መንፈስ ያላበሰ የሀገር ኩራት ነው" ብለዋል።

ለግድቡ ግንባታ መሳካት በክልሉ የሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እና ህዝቡ ያደረገው አስተዋጾ ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰው፣ በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰባሰቡን ገልጸዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ለሕዳሴው ግድብ በተለያየ መንገድ ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ሲወጣ መቆየቱን ያነሱት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው በውሃው ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን አቅም በመጠቀም ምሁራንን በማስተባበር የተለያዩ ጥናትና ምርምሮች ከማድረግ ባለፈ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ግድቡን በሚመለከት የተለያዩ መድረኮች ሲያዘጋጅ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በቀጣይም የግድቡ ግንባታ ሥራ እስኪጠናቀቅ ድረስ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አረጋግጠዋል።

ባለፉት 13 ዓመታት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተደረገ ህዝባዊ ድጋፍ 19 ነጥብ 14 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡ ከብሔራዊ ምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም