ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የዲጂታል ሽግግር ለማሳካት የግሉ ዘርፍ የመሪነት ሚና መወጣት አለበት

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2016(ኢዜአ)፡-  የኢትዮጵያን የዲጂታል ሽግግር ለማሳካት የግሉ ዘርፍ የመሪነት ሚና መወጣት እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ። 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ሚኒስትሮችና የቴክኖሎጂ ዘርፉ ባለድርሻዎች በተገኙበት የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ነው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽን አይቀሬ በመሆኑ ወሳኝ ኢኒሼቲቮችን ቀርፃ መተግበር ጀምራለች ብለዋል።

ለኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽንን ማፋጠን የግድ የሆነባቸው ምክንያቶች አሉ ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አንደኛው ዲጂታላይዜሽን ዕድገትን የሚያፋጥን በመሆኑ ነው ብለዋል። 

ሁለተኛው መንግሥታዊ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እንደሚያግዝ ታምኖ መሆኑን ገልፀዋል። 


 

ሦስተኛው ማኅበረሰባዊ ጠቀሜታው የላቀ እንደሆነ ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት የሚያስችል እምቅ ፀጋ እንዳላት ጠቅሰው፤ ለአብነትም ለቴክኖሎጂ ፈጠራ ቅርብ የሆኑ በርካታ ወጣቶች ያሉባት መሆኑን ገልፀዋል። 

በፖሊሲ ደረጃ በአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ አይ ሲ ቲ ከአምስቱ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ ሆኖ እየተሠራበት እንደሚገኝ አንስተዋል። 

በመሠረተ-ልማትም በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል። 

የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ በ2025 ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑንም አንስተዋል። 

አካታች ኢኮኖሚን ለመገንባትም ዲጂታል ጉዞው ትልቅ ሚና እንደሚወጣ ተናግረዋል። 

መንግሥት ለዘርፉ እውን መሆን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት አቋቁሞ  ወደ ሥራ መግባቱን አንስተው፤ የመጀመሪያው ዓላማ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማሳደግ ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር መሆኑን ተናግረዋል። 

ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማፋጠን በራስ አቅም ያሉ ፀጋዎችን በቅንጅት ወደ ጥቅም እንዲቀየሩ ማድረግም ትኩረቱ ነው ብለዋል። 

ሌላኛው ዓላማ በመንግሥት ተቋማት ወጪ ቆጣቢ አሠራር እንዲተገበር ማድረግ መሆኑንም ገልፀዋል።

በአገራዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ የግሉ ዘርፍ ግንባር ቀደም ተዋናይ እንዲሆን ይጠበቃል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም