ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የመገናኛ ብዙሃን የላቀ ሚና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል- አቶ እውነቱ አለነ - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የመገናኛ ብዙሃን የላቀ ሚና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል- አቶ እውነቱ አለነ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2016(ኢዜአ)፦ ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የመገናኛ ብዙሃን የላቀ ሚና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን "የኢትዮጵያ ሚዲያ ለኢትዮጵያውያን ውጤታማ ሀገራዊ ምክክር" በሚል መሪ ሃሳባ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የስራ ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች ጋር ውይይት እያደረገ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ፤ ለኮሚሽኑ ጥረት መሳካት የመገናኛ ብዙሃን ሚና ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል።
በመሆኑም ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የመገናኛ ብዙሃን የላቀ ሚናቸው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐመድ ድሪር፤ ኢትዮጵያ ችግሮቿን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
የምክክር ሂደቱ አሁን ላይ በ10 ክልሎች እና በ2 የከተማ መስተዳድሮች 17 ሺህ 210 ተወካዮች የተመረጡ ሲሆን የተሳታፊ ልየታ መጠናቀቁንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን መሰረታዊ ችግሮች በምክክር በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት መገናኛ ብዙሃን የማይተካ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
በእስካሁኑ ሂደት መገናኛ ብዙሃን ለነበራቸው አስተዋጽኦ አመስግነው በቀጣይም የላቀ ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱን በቅርቡ ከአዲስ አበባ ጀምሮ ወደ ሌሎችም አካባቢዎች የሚቀጥል ሲሆን አስካሁን ከ6 ሺህ 215 በላይ ተባባሪ አካላት ጋር መስራቱ ተመላክቷል።