ቀጥታ፡

ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የደቡብ ደቡብ ትብብር ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2016(ኢዜአ)፡- ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የደቡብ ደቡብ ትብብር ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ። 

ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄደው ጉባኤ "የደቡብ ደቡብ ጉባኤ ዓለም አቀፍ የደቡብ ትብብርን በዘላቂነት ያሳድጋል" በሚል መሪ ሃሳብ ነው።

በጉባኤው የተለያዩ አገራትንና ዓለም አቀፍ ተቋማትን የወከሉ አካላት ተገኝተዋል። 

በጉባኤው ያልተማከለ የታዳሽ ኃይል አጠቃቀም፣ ዘላቂ የልማት ተሞክሮን፣ ፈጠራና እውቀትን በመጋራት ዓለም አቀፍ ደቡብ ደቡብ ትብብር ለማጎልበት ያለመ መሆኑ ተገልጿል። 

ዓለም አቀፍ አጋሮችን፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የቴክኖሎጂና ስራ ፈጣሪዎች፣ ባለሃብቶች፣ ምሁራን ጨምሮ ጉባኤው ከ500 በላይ ተሳታፊዎችን የሚያሰባስብ እንደሆነ ተገልጿል።

ከአፍሪካ አገራትና ከህንድ የመጡ ሙያተኞችም በፀኃይ የኃይል የሚሰሩ የታዳሽ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ግኝቶቻቸውን የሚያሳዩበት ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ተዘጋጅቷል። 

በጉባኤውም ያልተማከለ የታዳሽ ኃይል አማራጭ ተደራሽ ያልሆኑ ማህበረሰቦችን ተጠቃሚነት ማሳደግ፤ የአየር ንብረትን የመቋቋም አቅም በመገንባት ሁሉን አቀፍ እድገትን ለማረጋገጥ የሚያበረክተውን ሚና የሚዳሰሱበት ይሆናል ተብሏል። 

የተገለሉ ማህበረሰቦችን በዘላቂነት በዕውቀት በቁሳቁስ ማብቃት፣ በታዳሽ የኃይል አማራጭ የተደገፈ ዘላቂ የኢኮኖሚያዊ የመተዳደሪያ ዕድልን መክፈት፣ የአየር ንብረትን የመቋቋም አቅም መገንባት፣ የባለድርሻ አካላትን ትብብር የሚያሳድጉ ውይይቶች ማመቻቸት የጉባኤው ዋና ዋና የትኩረት መስኮች መሆናቸው ተመላክቷል። 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም