በኢትዮጵያ የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተደረገ ባለው ጥረት የልማት አጋሮች ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተደረገ ባለው ጥረት የልማት አጋሮች ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተደረገ ባለው ጥረት የልማት አጋሮች ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የግብርና ሚኒስቴር ጠየቀ።
በኢትዮጵያ የወተት ምርት እሴት ሰንሰለትን ማሻሻል በሚቻልባቸው አማራጮች ላይ ያተኮረ የባለድርሻ የምክክር አውደ-ጥናት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
አውደ-ጥናቱን ያዘጋጁት የግብርና ሚኒስቴር ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) እና ከኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) ጋር በመተባበር ነው።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ባላት የእንስሳት ኃብት ልክ እስካሁን ተጠቃሚ ሳትሆን ቆይታለች ብለዋል።
በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር በእንስሳት ዘርፍ ያለውን ምርታማነት ከማሳደግ ባለፈ የአርሶና አርብቶ አደሮችን መነሳሳት መፍጠሩን ተናግረዋል።
በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር እስከ 2016 በጀት ዓመት ማብቂያ 9 ነጥብ 8 ቢሊየን ሊትር ወተት ለማምረት መታቀዱን ገልፀዋል።
በወተት ልማት ስትራቴጂው አማካኝነት ምርታማነቱን በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2030 ወደ 28 ነጥብ 4 ቢሊየን ሊትር ለማሳደግ መታቀዱን ጠቁመዋል።
በዘርፉ ልማት የተጀመሩ ሥራዎች ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን የወተት ምርት ሙሉ ለሙሉ የሚያስቀርና ለውጭ ገበያ ለማቅረብም የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተደረገ ባለው ጥረት የልማት አጋሮች ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) የኢትዮጵያ ተወካይ ፋራይ ዚሙድዚ፤ ድርጅቱ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) የኢትዮጵያ ቢሮ ዳይሬክተር ሃን-ዴኦግ ቾ፤ ኤጀንሲው የግብርና ዘርፉን ለመደገፍ በተለይ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮችን ለመደገፍ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ የወተት ምርት እሴት ሰንሰለት ላይ ያለውን የአመራረትና አያያዝ ችግር ለመፍታት የ10 ሚሊየን ዶላር መርሃ-ግብር መቅረጹንም አስረድተዋል።
የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር እስከ 2018 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን፤ በመርሃ-ግብሩ አማካኝነት የወተት ምርትን 6 ነጥብ 9 ቢሊየን ሊትር ዓመታዊ ምርት ወደ 11 ነጥብ 7 ቢሊየን ሊትር ከፍ ለማድረግ መታቀዱን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በመርሃ-ግብሩ የዶሮ እርባታን በማሻሻል የእንቁላል ምርትን ከ3 ነጥብ 2 ቢሊየን ወደ 9 ነጥብ 1 ቢሊየን እንዲሁም የዶሮ ሥጋ ምርትን ደግሞ ከ90 ሺህ ቶን ወደ 240 ሺህ ቶን ለማድረስ ታልሟል።
በተጨማሪም የማር ምርትን ከ147 ሺህ ቶን ወደ 296 ሺህ ቶን ለማሳደግ በመርሃ-ግብሩ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል።