የቱሪዝም ኃብትን የሀገር የኢኮኖሚ እድገት መሠረት ለማድረግ የተጀመረው ጥረት የሚደነቅ ነው- ምክር ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
የቱሪዝም ኃብትን የሀገር የኢኮኖሚ እድገት መሠረት ለማድረግ የተጀመረው ጥረት የሚደነቅ ነው- ምክር ቤቱ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2016(ኢዜአ)፦ የቱሪዝም ልማትን በማስፋትና በማዘመን የሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት ለማድረግ የተጀመረው የተቀናጀ ጥረት የሚደነቅና ሊበረታታ የሚገባው መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቱሪዝም ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።
የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፤ የተቋሙን አጠቃላይ አፈጻጸም በተመለከተ ለምክር ቤቱ ዝርዝር ሪፖርት አቅርበዋል።
በዘጠኝ ወራት 861 ሺህ 126 የውጭ አገራት ቱሪስቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ጉብኝት ማድረጋቸውን ገልፀዋል።
በተጠቀሰው ወራት ከውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር መገኘቱን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
በተለይም የአገር ውስጥ ጉብኝት ባህል ማደጉ እና በ "ልወቅሽ ኢትዮጵያ" ንቅናቄ ለዘርፉ ትልቅ መነቃቃት መፍጠሩንና አመርቂ ውጤት መገኘቱንም አንስተዋል።
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 30 ነጥብ 5 ሚሊየን የአገር ውስጥ ጎብኝዎች ተንቀሳቅሰው 48 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ስለመገኘቱም ገልፀዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተገነቡት የገበታ ለሸገር እና ገበታ ለሀገር የተሰሩ የቱሪዝም መዳረሻዎች ለዘርፉ እድገት የላቀ አስተዋጽዖ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።
የኢኮ-ቱሪዝም እና ፓርኮችን የመጠበቅና የማልማት ሥራዎችም በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።
በምክር ቤቱ የንግድና የቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አሻ ያህያ፤ የቱሪዝም ልማትን የሀገር ኢኮኖሚ መሠረት ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች የሚደነቁ ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ እምቅ የቱሪዝም ኃብት ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤ የዘርፉን ልማት በማስፋትና በማዘመን የሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት ለማድረግ የተጀመረው የተቀናጀ ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልፀዋል።
በተለያዩ አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን እምቅ የቱሪዝም ኃብቶች የማስተዋወቅና የገጽታ ግንባታ ሥራም ትኩረት ሊደረግበት ይገባል ብለዋል።
በፓርኮች የሚስተዋለውን ሕገ-ወጥ ተግባር በዘላቂነት ለማስቆም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።