ቀጥታ፡

የፖሊስን አሰራር በጥናት በማስደገፍና ይበልጥ በማዘመን ለዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት የመስጠት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2016(ኢዜአ)፦ የፖሊስን አሰራር በጥናት በማስደገፍ፣ ዘመናዊና ይበልጥ ተደራሽ በማድረግ ለዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት የመስጠት ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መስፍን አበበ ገለጹ።

6ኛው ሀገር አቀፍ የፖሊስ ምርምር ሲምፖዚየም በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ መካሄድ ጀምሯል።


 

ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው መድረክ የመከላከያና የፖሊስ መኮንኖች፣ የተቋማት የስራ ኃላፊዎችና ሌሎችም ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መስፍን አበበ፤ የሲምፖዚየሙ ዓላማ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በመቀመር ፖሊሳዊ አሰራርን ለማሻሻል ነው ብለዋል።

ለሙያው አጋዥ የሆኑ ጥናትና ምርምሮችን በማጋራት ዘመናዊ የአሰራር ስርአት ለመዘርጋት የሚያግዝ መሆኑንም ገልጸዋል።

የፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በሁሉም መልኩ በስኬታማ ጉዞ ላይ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም የጥናትና ምርምር ስራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የፖሊስን አሰራር ዘመናዊና ይበልጥ ተደራሽ በማድረግ ለዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት የመስጠት ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተፈሪ ጥያሩ፤ ዘመናዊ አሰራር፣ ጠንካራ አደረጃጀትና በሁሉም ረገድ የተሟላ ቁመና ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት በኢንስቲትዩቱ አስፈላጊው እገዛ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

የሲቪል ሰርቪስ ዪኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚደንት አለማየሁ ደበበ (ዶ/ር)፤ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ለፖሊሲ ግብዓትነት መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።


 

የጥናትና ምርምር ውጤቶች በሚወጡ ፖሊሲዎች ላይ በጎ ተጽዕኖ በማሳደር የማህበረሰብን ህይወት የመለወጥ ተልዕኮን መወጣት እንደሚኖርባቸውም ገልጸዋል።  

በነገው እለትም ቀጥሎ በሚውለው መድረክ በድንበር ተሻጋሪ ስደትና በሰዎች መነገድ፣ የግጭት አስተዳደርና ተፈጥሯዊ ሁኔታ፣ የግጭት መነሻና የሠላም ግንባታ ጉዳይ በስፋት የሚመከርበት ይሆናል።

የመንገድ አስተዳደር የትራንስፖርት ደኅንነት ትራፊክና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር እየተደረገባቸው ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም