ቀጥታ፡

በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አለምአቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ዘርፉን በሰለጠነ የሰው ሀይልና ቴክኖሎጂ ለመደገፍ እየተሰራ ነው

 አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2016(ኢዜአ)፦ በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ  ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ዘርፉን በሰለጠነ የሰው ሀይልና ቴክኖሎጂ የመደገፍ ስራ እየተከናወነ ነው።

የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችና ላኪዎች ማህበር በኦንላይን ስልጠና መስጠትና የእውቀት አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።

ማህበሩ ስምምነቱን የተፈራረመው ትሬድ ማርክ አፍሪካና አዳፕቲቭ ዳታ ፊዥን ሲስተምና ኢንዴክስ አይቲ ቴክኖሎጂ ከተባሉ ድርጅቶች ጋር ነው።

የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ዘውዴ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኢትዮጵያ በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ያላትን እምቅ አቅም አሟጦ ለመጠቀም ዘርፉን በሰለጠነ የሰው ሃይልና ቴክኖሎጂ መደገፍ ወሳኝ ነው።


 

ጥራት ያላቸው ምርቶች ወደ ውጪ ለመላክና በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን አዳዲስ አሰራሮችን መተግበርና የሰው ሀይሉን ማብቃት እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።

ዘርፉ ለሀገሪቷ አጠቃላይ አመታዊ ዕድገት ያለውን ድርሻ የበለጠ ለማሳደግ ከእርሻ ጀምሮ ምርቱ ለገበያ እስኪቀርብ ያለውን ሰንሰለት በእውቀት መምራት ተገቢ መሆኑንም ነው ያነሱት።

በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች በተበታተነ ቦታ ላይ የሚገኙ በመሆኑ ለሁሉም አመቺ በሆነ መልኩ  የኦንላይን ስልጠናዎችን ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑንም አስረድተዋል።

ዘርፉን በሰለጠነ ሰው ሃይልና ቴክኖሎጂ የመደገፉ ስራ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተያዘው እቅድ አካል መሆኑንም አንስተዋል።

ማህበሩ ከራሱ ባለሙያዎች ባለፈ በዘርፉ ፍላጎት ያለው ማንኛውም ዜጋ በቀላሉ ስልጠናዎችን ማግኘት የሚችልበትን ዕድል መፍጠሩን በመግለጽ።

የትሬድ ማርክ አፍሪካ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር እውነቱ ታዬ በበኩላቸው፣የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን የንግድ ትስስር ማሳለጥ የሚያስችሉ አሰራሮችን መዘርጋት ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው ብለዋል።


 

ተቋማቸው በተለይም የኢትዮ-ጅቡቲ የንግድ ኮሪደርን የንግድ እንቅስቃሴን ማቀላጠፍ የሚያስችሉ ዘመናዊ አሰራሮች እንዲዘረጉ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች አዳዲስ እውቀቶችን ማግኘትና ተወዳዳሪነታቸውን ማስፋት እንዲችሉ ሙያዊ ስልጠናዎችን መስጠት ተገቢ መሆኑን በማንሳት፡፡

የትሬድ ማርክ አፍሪካ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር እውነቱ ታዬ ዘርፉ ለስራ ዕድል ፈጠራ፣ለውጭ ምንዛሬ ግኝት እንዲሁም ለቴክኖሎጂ ሽግግር ያለውን ሚና የበለጠ ለማሳደግ አዳዲስ አሰራሮችን መዘርጋት ወሳኝ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ የአበባ ፣አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ዋነኛ የገበያ መዳረሻ የአውሮፓ ሀገራት ቢሆኑም ሀገራቱ ከጥራት ጉድለት ጋር ተያይዞ የተለያዩ እገዳዎችን እንደሚጥሉ ነው ሃላፊዎቹ የገለጹት።

ጥራቱን የጠበቀና አለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ለማምረት ባለሙያዎችን በየጊዜው ማሰልጠንና አሰራሮችን በቴክኖሎጂ መደገፍ እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።

የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችና ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ዘውዴ እንደገለጹት ዘርፉ ለሌሎች ኢንዱስትሪዎች ግብዓት ከማቅረብ ባለፈ ሀገሪቱ ከገቢ ግብር የምታገኘው ሀብት እንዲጨምር እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

የኦንላይን ስልጠናና የእውቀት አስተዳደር ስርአቱን ለማበልጸግና ወደ ስራ ለማስገባት የአውሮፓ ህብረት የ350 ሺ ዶላር ድጋፍ ማድረጉም ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም