የኢትዮጵያ 15 በመቶ የሚሆነው የገቢ ወጪ ጭነት በኢትዮ -ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አማካይነት እየተከናወነ ነው 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ 15 በመቶ የሚሆነው የገቢ ወጪ ጭነት በኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አማካይነት እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) አጠቃላይ የተቋሙን የስራ እንቅስቃሴ አስመልክተው ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በዚህም ከመንገደኞች አገልግሎት አንጻር በየዓመቱ 30 በመቶ እድገት እያስመዘገበ መምጣቱን ገልጸዋል።

ማህበሩ አሁን ላይ ጭነት የማመላለስ አቅሙ ከ 2 ነጥብ 1 ሚልዮን ቶን በላይ መድረሱን ተናግረዋል።

ማህበሩ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ገቢው ከ 800 ሺህ ብር እንደማይበልጥ በማስታወስ አሁን ላይ የገቢ አቅሙ ወደ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ማደጉን ጠቁመዋል

ማህበሩ 40 በመቶ የሚጠጋ አቅሙን እየተጠቀመ መሆኑን በመግለጽ አሁን ላይ አገልግሎቱን በእጥፍ ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ 15 በመቶ የሚሆነው የገቢ ወጪ ጭነት በኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አማካይነት እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

98 በመቶ የቡና ምርት እንዲሁም መቶ በመቶ የምግብ ዘይት የሚጓጓዘው በባቡር ትራንስፖርት እንደሆነ ገልጸዋል።

ማህበሩ በሙሉ አቅሙ መንቀሳቀስ ሲጀምር በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አረጋግጠዋል፡፡

በቀጣይ በማዕድን ዘርፍ የድንጋይ ከሰል እና ሲሚንቶ ማጓጓዝ እንደሚጀምር አስታውቀዋል።

ማህበሩ የተለያዩ ዘርፎችን በመደገፍ እና የተለያዩ ምርቶችን የመጫን አቅሙን በማስፋት በርካታ አካላት ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር እንዲገቡ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

እንዲሁም የመንገደኞች አገልግሎትን በማስፋት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር የሚረዳ  አስተዋጽኦ ለማበርከት ማቀዱን አንስተዋል። 

በኤሌክትሪክ ሀይል የሚሰራው እና ከአየር ብክለት ነፃ የሆነው የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር 752 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም