የመምህራን መኖሪያ ቤት ችግርን መፍታት በሥራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የመምህራን መኖሪያ ቤት ችግርን መፍታት በሥራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ተገለጸ
አዳማ፣ግንቦት 13/2016 (ኢዜአ)፡-የመምህራን መኖሪያ ቤት ችግርን መፍታት ለመማር ማስተማር ሥራ ውጤታማነት አጋዥ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ ገለፁ።
1ሺህ 150 ለሚሆኑ መምህራን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተሰጥቷል።
የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ቶላ በሪሶ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለፁት ትውልድን በዕውቀት ለመቅረፅ የመምህራን የኑሮና የመኖሪያ ቤት ችግር መፍታት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።
የመምህራን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት የክልሉ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
የመምህራን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ፣ የትምህርት ቤቶች ይዞታ ማስከበርና ትምህርት ቤቶች የራሳቸውን ገቢ ማመንጨት እንዲችሉ በማድረግ ረገድ ደግሞ ሌሎች ከተሞች ከአዳማ ምሳሌ መውሰድ አለባቸው ብለዋል።
በክልሉ "4ሺህ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ስራ ተሰርቷል" ያሉት ዶክተር ቶላ፤ ይህም ምቹ የመማሪያ ቦታ በመፍጠሩ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል።
የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው አስተዳደሩ የከተማዋን መምህራን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራት በማከናወን ላይ ነው ብለዋል።
በተለይም መምህራን የተረጋጋ ህይወት ኖሯቸው ብቁ ትውልድ ለማፍራት እንዲችሉ አስተዳደሩ ከተማሪዎች ቤተሰብ፣ ከተማሪዎችና መምህራን ጋር የተቀናጀ ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም የመምህራን የመኖሪያ ቤት እጦትና የገበያ ዋጋ ንረት የሚያሳድረውን ጫና ለመፍታት የሚያግዙ ተግባራት እየተሰሩ መሆናቸውን አክለዋል።
አስተዳደሩ የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል በሙሉ አቅሙ እየሰራ መሆኑን ተናግረው፤ ዛሬ ለመምህራን የተላለፈው መሬት በህገ ወጥ ግንባታ የተያዘ መሬት መሆኑን ከንቲባው ጨምረው ገልፀዋል።
"በአዳማ በህዝብ፣ በባለሃብቶችና በአስተዳደሩ የተቀናጀ ተሳትፎ 315 ትምህርት ቤቶችን የማደስና ደረጃ የማሻሻል ስራ ተሰርቷል" ያሉት ደግሞ የአዳማ ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ በሪሶ ዶሪ ናቸው።
በከተማዋ 36 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች በ266 ሚሊዮን ብር ወጪ መገንባቱን የገለፁት አቶ በሪሶ፤ በቅርቡም 10 ቅድመ መደበኛ፣ ሶስት የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገነባሉ ብለዋል።
ዛሬ 1ሺህ150 ለሚሆኑ መምህራን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ መሰጠቱን የገለፁት ሃላፊው፤ በእስከ አሁኑ ሂደት ከ2ሺህ 600 በላይ መምህራን በከተማዋ የመኖሪያ ቤት ቦታ መሰጠቱን አስታውሰዋል።
የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ካገኙት መምህራን መካከል መምህርት ኑስ ኮርሜ እንዳሉት በነበረባቸው የመኖሪያ ቤት ችግር ቤተሰቦቻቸውን ይዘው በኪራይ ቤት ሲሰቃዩ እንደነበር ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት አስተዳድሩ የመምህራንን ችግር ተገንዝቦ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ በመስጠቱ "በተረጋጋ መልኩ የመማር ማስተማር ስራችንን ለማከናወንና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የድርሻችንን እንድንወጣ ያስችለናል" ብለዋል።