ለመጀመሪያው ዙር የሐጅ ተጓዦች በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሽኝት ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ለመጀመሪያው ዙር የሐጅ ተጓዦች በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሽኝት ተደረገ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2016(ኢዜአ)፦ ለዘንድሮው ለ1 ሺህ 445ኛው የሐጅ ስነ-ስርአት የመጀመሪያ ዙር ተጓዦች በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሽኝት ተደረገ።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራርና ሰራተኞች በተገኙበት ሽኝቱ መደረጉ ታውቋል።
የጠቅላይ ምክር ቤቱ ዋና ጸሃፊ ሸኽ ሃሚድ ሙሳ፤ በሂደቱ የምዝገባ፣ የቪዛ፣ የምክርና ተያያዥ አገልግሎቶች በተቀላጠፈ መልኩ መሰጠታቸውን ገልጸዋል።
ለሃጅ ስነ ስርአቱ ከጉዞ እስከ መመለሻ ድረስ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በባለፈው አመት 11 ሺህ ሑጃጆች መጓዛቸውን አስታውሰው ዘንድሮ ደግሞ ከ12 ሺህ በላይ ተጓዦች ወደ ስፍራው የሚያቀኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት በዛሬው እለት የመጀመሪያው ዙር የሁጃጆች የሽኝት ስነ ስርአት መደረጉን ተናግረዋል።
ለጉዞው መሳካት የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ ባንኮችና ሌሎችም አካላት ለነበራቸው የላቀ ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።
የሁጃጆች ጉዞ ለአንድ ወር የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመው የተጀመረው አገልግሎትና ቀልጣፋ መስተንግዶ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።