አሳታፊ የሀገረ መንግስት ግንባታን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
አሳታፊ የሀገረ መንግስት ግንባታን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12/2016(ኢዜአ)፦ የውይይት ባህልን በማጎልበት አሳታፊ የሀገረ መንግስት ግንባታን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን(ዶ/ር) ንግግሮችና መልዕክቶች የያዘና ''ከመስከረም እስከ መስከረም'' የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ በቅቷል።
በወዳጅነት ፓርክ በተካሄደው የመጽሐፉ ይፋ ማድረጊያ መርሐ ግብር ላይ ሙያዊ ውይይት ተደርጓል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት የተዘጋጀው ይህ መጽሐፍ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመስከረም 24 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ መስከረም 24 ቀን 2016 ዓ.ም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ላይ ያደረጓቸው 91 ንግግሮችና መልክቶችን ያያዘ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት ሃላፊ ቢልለኔ ስዩም በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ መጽሐፉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር የያዘ 6ኛው መድብል መሆኑን ገልጸዋል።
የመሪ ታሪክ የሀገር ታሪክ አካል መሆኑን ጠቅሰው፣ ከዚህ አኳያ መጽሐፉ ለታሪክ አጥኝዎች፣ ለፖሊሲ አውጭዎችና ለፖለቲካ ተመራማሪዎች በመረጃ ግብዓትነት እንደሚያገለግል አብራርተዋል።
በመድረኩም ተማሪዎች ከመጽሐፉ የተመረጡ ገጾችን እንደ ውይይት መነሻ ሃሳብ በንባብ አቅርበዋል።
ከእነዚህ መካከል ተማሪ ኤፍሬም አጽብሃ እና ተማሪ ሲያም ዱላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ጊዜያት ሰላምን በሚመለከት ያደረጓቸውን ታሪካዊ ንግግሮች አቅርበዋል።
በተማሪዎች በንባብ የቀረቡ መልዕክቶች ላይም በተሳታፊዎች ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ በዚህም በመጽሃፉ የተሰነዱት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግሮች ዘላቂ ሰላም፣ ልማት፣ ፍትሐዊነትና ዴሞክራሲ መስፈን ላይ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውን ነው ተሳታፊዎች ያነሱት።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና እስያ ጥናት ማዕከል ተመራማሪው ሳሙኤል ተፈራ (ዶ/ር)፣ በመጽሐፉ የተሰነዱ መልዕክቶች ጥላቻና መከፋፈል የኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንቅፋት መሆናቸውን አጽንዖት የሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በአካል በመገኘት ለዘላቂ ሰላም እውን መሆን በተግባር መስራታቸውን በመጥቀስ፤ ይህም በመጽሃፉ የተሰነዱ ሃሳቦች ወደ ተግባር እየተቀየሩ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ለመጪው ትውልድ የተሻለች አገር መገንባት ላይ የሁሉም ዜጋ ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
የውይይት ባህልን በማጎልበት አሳታፊ የሀገረ መንግስት ግንባታ እውን ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም እንዲሁ፡፡
በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት ትህትና ለገሰ በበኩላቸው፣ በመጽሐፉ የተሰነዱ መልዕክቶች ሀገርን ወደ ተሻለ ነገ የማሸጋገሩ ስራ በትውልድ ቅብብሎሽ እንደሚከናወን የሚያመላክቱ ስለመሆናቸው ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ መጽሐፉ ከየት ተነስትን የት መድረስ እንዳለብን መነሻ የሚሆኑ መንገዶችን የሚያመላክት ነው ብለዋል።
በተለይ በተቋም ግንባታ ላይ የቀረቡ ሃሳቦች አሁን ላይ በተግባር እየተቀየሩ ስለመሆናቸውም ነው የጠቆሙት፡፡
''ከመስከረም እስከ መስከረም'' መጽሐፍ በ415 ገጾች የተደራጀ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ እንግሊዝኛ እና በአረብኛ ቋንቋዎች ያስተላለፏቸውን መልዕክቶች ይዟል።