አፍሪካውያን ሰላም የሰፈነባትና የበለፀገች አህጉርን ዕውን ለማድረግ የፀጥታና ደህንነት ትብብራቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል- ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካውያን ሰላም የሰፈነባትና የበለፀገች አህጉርን ዕውን ለማድረግ የፀጥታና ደህንነት ትብብራቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል- ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12/2016(ኢዜአ)፦ሰላም የሰፈነባትና የበለፀገች አፍሪካን ዕውን ለማድረግ ሀገራት የፀጥታና ደህንነት ትብብራቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ ገለጹ፡፡
በመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት 61ኛው የአፍሪካ ቀን በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተከብሯል፡፡
በዓሉ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ አፍሪካ ህብረት ከ61 ዓመታት በፊት እ.አ.አ ግንቦት 25/1963 የተመሰረተበትን ቀን ለማሰብ በየዓመቱ ይከበራል።
የመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ በዚሁ ወቅት፤ ፓን አፍሪካኒዝም አንድነቷ የጠነከረና ችግሮቿን በራሷ የምትፈታ አህጉርን እውን የማድረግ ትልም መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ሂደትም የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ተመስርቶ ንቅናቄውን በተቋማዊ ህብረት ወደፊት ለማራመድ ጥረት ማድረጉን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረትና በተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ስር በቀጣናውና በአህጉሪቱ ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ሚና እየተወጣች መሆኗን አንስተዋል።
ሰላም የሰፈነባትና የበለፀገች አፍሪካን እውን ለማድረግ አፍሪካውያን አንድነትና ትብብራቸውን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጠናከር እንዳለባቸው ነው ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ የጠቆሙት።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በሚለው መርህ ለአህጉሪቱ ሰላምና መረጋጋት የምታደርገውን ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ አምባሳደር ጀማሉዲን ሙስጠፋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት የያዛቸው ግቦች እንዲሳኩ የበኩሏን ጥረት እያደረገች መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለአህጉሪቱ ፀጥታና ደህንነት መጠበቅ እንዲሁም ለሀገራት ሰላም ወታደሮቿን በቀዳሚነት በማሰማራት ተጠቃሽ ሀገር መሆኗንም አክለዋል።
በቀጣይም የአፍሪካን አንድነትና ሰላም ለሚያጸኑ አፍሪካዊ መፍትሔዎች ተፈጻሚነት ብርቱ ጥረቷን ትቀጥላለች ብለዋል።
በአውደ ጥናቱ ላይ ጽሑፍ ያቀረቡት የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ፣ የፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ከፍተኛ መኮንን፥ ኮሎኔል ሼኩ ቲጋን፥ ግንቦት 25/1963 የአፍሪካ አንድነት መስራች አባቶች ራዕይ እውን የሆነበት ነው ብለዋል።
ቀኑ አፍሪካ በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ወደተሻለ ምዕራፍ እንድትሸጋገርና ህዳሴዋን እንድታረጋግጥ መሰረት የተጣለበት መሆኑንም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የሴራሊዮን ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ የሆኑት ብርጋዴር ጀነራል አቡበከር ኩንቴ፥ የኢትዮጵያ ሰራዊት የአፍሪካ ቀንን ማክበሩ ለአፍሪካውያን ትልቅ ትርጉም የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት እውን መሆንና ለሀገራት ሰላም በረጅም ዘመን ያበረከተችው አስተዋፅኦ መላው አፍሪካውያንን የሚያኮራ መሆኑንም አንስተዋል።
በዚህ ሂደት የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ የከፈለው ዋጋ በአፍሪካ ሰላም ማስከበር ታሪክ ትልቅ አሻራ ያለው ነው ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አመራሮች፣ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች፣ የአፍሪካ ህብረት ተወካዮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።