የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሐጅና ዑምራ ተጓዦችን ለማስተናገድ ዝግጅቱን አጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሐጅና ዑምራ ተጓዦችን ለማስተናገድ ዝግጅቱን አጠናቋል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ1445ኛውን የሐጅና ዑምራ ተጓዦችን ለማስተናገድ ዝግጅት ማጠናቀቁን የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ የዘንድሮው የሐጅና ዑምራ ጉዞን የተሳካ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል።
አየር መንገዱ ከቅድመ በረራ ክፍል ጀምሮ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸው፤ ይህንን ሃይማኖታዊ ጉዞ የሚያሳልጡ ሠራተኞችን መመደባቸውንም ነው የጠቆሙት።
አንድ ወር በሚቆየው በዚህ ጉዞ 12 ሺህ ሃይማኖታዊ ጉዞ የሚያደርጉ መንገደኞችን ወደ ሥፍራው ወስዶ ለመመለስ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው፤ አየር መንገዱ ለሐጅና ዑምራ ጉዞ መሳለጥ ከፍተኛ ትብብር እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል።