ቀጥታ፡

በወጣቶች ዙሪያ የሚሰሩ የመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፎረም ተመሰረተ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12/2016 (ኢዜአ)፦የወጣቶችን  ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በወጣቶች ዙሪያ የሚሰሩ የመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፎረም ተመሰረተ።

ፎረሙን የመሰረቱት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት በጋራ በመሆን ነው።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የአሰራር ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል። 

ፎረሙ የወጣቶችን ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማሳደግና በተደራጀና በተናበበ መልኩ ሀብት ለማሰባሰብ ይረዳል ብለዋል፡፡

በተጨማሪ ወጣቶች በሀገር ልማትና ሰላም ዙሪያ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ፣ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን በፋይናንስ  በመደገፍ  የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።

ፎረሙ የወጣቶችን መልካም ስነ ልቦና በመገንባት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተሰማርተው ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉ እንደሚያስችል ጠቅሰዋል፡፡


 

ወጣቶች አዳዲስ ሀሳቦችን በማፍለቅ የበለፀገች ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተመላክቷል። 

በዚህም ወጣቶችን በማህበራዊና በኢኮኖሚ ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በቅንጅትና በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

ወጣቶች የሚደረግላቸውን ድጋፍ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለሀገር ልማትና ሰላም  የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት  እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የፎረሙ አላማዎች እንዲሳኩ ሁሉም በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅበታል ሲሉ አሳስበዋል።

የአክሸን ኤድ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ተወካይ አቶ ጣሰው እንዳለ የተመሰረተው ፎረም ሀብትንና እውቀትን በተደራጀ መልኩ በመጠቀም ወጣቶችን ለመደገፍ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

አክሽን ኤድ በፎረሙ የተቀመጡ አላማዎች እንዲሳኩ በትብብርና  በቅንጅት እንደሚሰራ ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት የወጣቶች ዘርፍ ሃላፊ ይሁነኝ መሃመድ ፎረሙ ወጣቶች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ጥያቄዎቻቸውን በተደራጀ መልኩ በማቅረብ ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ ዕድል የሚፈጥር እንደሆነ ተናግሯል።

የምክር ቤቱ አባላት በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመታገዝ ለአገር ልማት፣ዕድገትና ሰላም የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ አረጋግጧል። 

የፎረሙን ምስረታና በቀጣይ የሚሰሩ ጉዳዮችን የሚያመላክት ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም