ባለፉት ዘጠኝ ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም በበጀት ዓመቱ ለማሳካት የታቀደውን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ እንደሚቻል ያመላከተ ነው-ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም በበጀት ዓመቱ ለማሳካት የታቀደውን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ እንደሚቻል ያመላከተ ነው-ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12/2016 (ኢዜአ)፦ የባለፉት ዘጠኝ ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም በበጀት ዓመቱ ለማስመዝገብ የታቀደውን የ7 ነጥብ 9 ኢኮኖሚያዊ እድገት ማሳካት እንደሚቻል ያመላከተ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋ፤ ሀገራዊ የዘጠኝ ወራት የልማት አፈፃፀምን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በማክሮ ኢኮኖሚ፣ በመሠረተ ልማትና በፕሮጀክቶች፣ በሪፎርም ሥራዎች እንዲሁም በሌሎች አበይት ጉዳዮች ላይ የተመዘገቡ ውጤቶችን ዘርዝረዋል።
ይህንንም ተከትሎ በግብርና ዘርፍ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ዋና ዋና ከሚባሉ ሰብሎች ከ100 ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ጠቅሰው ከ6 ነጥብ 58 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ መሸፈኑን ተናግረዋል።
ከእንስሳት ኃብት አኳያ የተሰሩ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልፀው በዘጠኝ ወራት ውስጥ 2 ቢሊየን ሌትር ወተት፣ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን እንቁላል፣ 200 ሺህ ቶን ሥጋና 110 ሺህ ቶን የማር ምርት መገኘቱን ገልጸዋል።
በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሻለ አፈፃጸም በዘጠኝ ወራት ውስጥ መመዝገቡን ተናግረው በተለይም ከግብዓት አቅርቦት አኳያ የተሻለ አፈጻጸም መኖሩን ጠቅሰው በዚህም የኢንዱስትሪውን አቅም የማሳደግ ሥራ ተሰርቷል ነው ያሉት።
በአገልግሎት ዘርፍ የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ያነሱት ሚኒስትሯ በትራንስፖርት ዘርፍ ለአብነት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የ25 በመቶ ብልጫ ማስመዝገቡን ጠቁመዋል።
በዲጂታል አገልግሎት፤ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 4 ትሪሊየን ብር መዘዋወሩን ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ ባለፋት ዘጠኝ ወራት በማክሮ ኢኮኖሚ የተመዘገበው አፈጻጸም በ2016 በጀት ዓመት ለማሳካት የታቀደውን የ7 ነጥብ 9 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ እንደሚቻል ያመላከተ ነው ብለዋል።