ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሥጋት የመሸከም አቅም ከ6 ትሪሊየን ብር በላይ ደርሷል 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሥጋት የመሸከም አቅም ከ6 ትሪሊየን ብር በላይ መድረሱን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነፃነት ለሜሳ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነፃነት ለሜሳ፤ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋስትና የመስጠት አቅሙን ለማሳደግ፣ አሠራሩን ለማዘመንና ተደራሽነቱን ለማስፋት ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ይህንንም ተከትሎ በ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ሥጋት የመሸከም አቅሙን በ50 በመቶ በማሳደግ 6 ነጥብ 2 ትሪሊየን ብር መድረሱን ገልፀዋል። 

በተመሳሳይ ተቋሙ ከአረቦን ገቢ 7 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ገልጸው፤ ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ33 በመቶ እድገት አሳይቷል ብለዋል። 

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ካሳ የከፈለ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ከታክስ በፊት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ትርፍ አስመዝግቧል።

  በሌላ በኩል የዘርፉ ተደራሽነት በሚፈለገው ልክ አለማደጉን አንስተዋል። 

ለዚህም የኢንሹራንስ ንቃተ-ህሊና አለማደግ፣ የቴክኖሎጂ ተደራሽነት ዝቅተኛ መሆን እንዲሁም በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን ያማከለ አለመሆን እንዳያድግ ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ ጠቅሰዋል።

አንዳንድ የዋስትና ዓይነቶች አስገዳጅ አዋጅ ቢኖራቸውም በተቋማት በኩል የመተግበር ክፍተት መኖሩን ጠቅሰው፤ በተሽከርካሪ መድህን በኩል መለዋወጫ ገበያው ላይ አለመኖርና የአደጋ መጨመር ኢንሹራንስ ኩባንያውን እየፈተኑ መሆኑን ገልፀዋል።

አያይዘውም እየደረሰ ላለው አደጋና እየተከፈለ ላለው ካሳ ተገቢውን አረቦን ለመጠየቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታትና ቀጣይ የሚሰሩ ሥራዎችን ለመደገፍ ገለልተኛ ኮሚሽን ለማቋቋም እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት አጠቃላይ የቅርንጫፎች ብዛት 125 የደረሰ ሲሆን፤ በቀጣይም ቅርንጫፎችን በማስፋትና ዘመናዊ አሠራርን በመዘርጋት ተደራሽነቱን ለማስፋት እየሰራ ይገኛል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም