የኢትዮጵያ ሴቶች ከ17 ዓመት በታች እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን ከአለም ዋንጫ ማጣሪያ ውጪ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሴቶች ከ17 ዓመት በታች እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን ከአለም ዋንጫ ማጣሪያ ውጪ ሆነ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ከ17 ዓመት በታች እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን በኬንያ አቻው ተሸንፎ ከአለም ዋንጫ ማጣሪያው ውጪ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ብሄራዊ ቡድኑ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ከኬኒያ አቻው ጋር ናይሮቢ ላይ አድርጎ 3 ለ0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።
ውጤቱንም ተከትሎ የኬንያ ብሄራዊ ቡድን ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።
የኬኒያ ብሄራዊ ቡድን በአራተኛው ዙር የብሩንዲ ብሔራዊ ቡድንን የሚገጥም ይሆናል።
አፍሪካ በዓለም ዋንጫው ሶስት አገራትን የማሳተፍ ኮታ ያላት ሲሆን 12 አገራት በውድድሩ ለመሳተፍ በሶስተኛው ዙር ማጣሪያ ጨዋታቸውን በማድረግ ይገኛሉ።
አዘጋጇ ዶሚኒካን ሪፐብሊክን ጨምሮ እንግሊዝ ፣ፖላንድ፣ ስፔን፣ ብራዚል፣ ኮሎምቢያ፣ ኢኳዶር፣ አሜሪካ፣ ሜክሲኮ፣ ኒውዝላንድ፣ ጃፓንና ሰሜን ኮሪያ ለዓለም ዋንጫው ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
16 ሀገራት የሚሳተፉበት 8ኛው የፊፋ ሴቶች ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ በዶሚኒካን ሪፐብሊክ አስተናጋጅነት ጥቅምት 2017 ዓ.ም ይካሄዳል።