በክልሉ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ ድጋፍና ክትትሉ ይጠናከራል - ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ ድጋፍና ክትትሉ ይጠናከራል - ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር)
ሚዛን አማን፤ ግንቦት 11/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ ድጋፍና ክትትሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የተመራና የዞንና የክልል የሥራ ኃላፊዎችን ያካተተ ቡድን በቤንች ሸኮ ዞን በፌዴራል መንግስት ድጋፍ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝቷል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በእዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ በክልሉ በፌዴራል መንግስት እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና የክልሉን የልማት ተስፋ ያሳደጉ ናቸው።
በግንባታ ሂደት ላይ ያለው የሚዛን አማን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እና የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት አካል የሆነው የደንቢ ሎጅ ከተጎበኙት ፕሮጀክቶች መካከል እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቶቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውሉ በክልሉ መንግስት የሚደረገው የድጋፍና ክትትል ሥራ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የሚዛን አማን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ገንባታ 62 በመቶ ላይ መድረሱን የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ የሚቀሩ ሥራዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ የግንባታ ሥራው የተጀመረውና የገበታ ለትውልድ አካል የሆነው የደንቢ ሎጅ የግንባታ ሂደት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
እንደ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ፣ የሎጁ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ በቀጣይ አምስት ወራት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለህዝብ ክፍት ይሆናል።
የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያን እየገነባ ያለው የ"ሳምሶን ቸርነት ጠቅላላ የሥራ ተቋራጭ" ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ኢዮብ ሞላ በበኩላቸው ግንባታውን ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለመጨረስ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የአየር ማረፊያው ግንባታ የህዝብ የልማት ጥያቄ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠውና ግንባታውን ለማፋጠን የሚያስፈልጉ ግብአቶች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ ሰኔ 10 ቀን 2013 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠው ወደ ሥራ መገባቱ ይታወቃል።