ቀጥታ፡

ኖርዌይ መንግስት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያከናውነውን ተግባር እንደምትደግፍ አስታወቀች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2016(ኢዜአ)፦  ኖርዌይ የኢትዮጵያ መንግስት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያከናውነውን የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ለመደገፍ  የጀመረችውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች።

ኖርዌይ እኤአ በ2011 ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በደርባን  ይፋ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ በዘርፉ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ጠንካራ አጋርነት መመስረቷ ይታወሳል።  

በኖርዌይ ኤምባሲ የአየር ንብረት፣ አካባቢና ደን አማካሪ ማሪ ማርቲንሰን ለኢዜአ እንዳሉት ኖርዌይ የኢትዮጵያ መንግስት በአየር ንብረትና በብዝሃ ህይወት ጥበቃ ላይ የያዘውን ግብ ለመደገፍ እየሰራች ነው።

በተጨማሪ አገራቸው በአየር ንብረትና በብዝሀ ህይወት ጥበቃ ዙሪያ የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የምርምር ማዕከላትን እየደገፈች መሆኗን ገልፀዋል። 

ኢትዮጵያ በብዝሀ ህይወት ጥበቃ ላይ በርካታ ተግባራትን እያከናወነች መሆኗን ጠቅሰው በተለይም በደን ጥበቃ ላይ እየተሰራ ያለው ስራ የሚበረታታ መሆኑንም ተናግረዋል። 


 

የኢትዮጵያ መንግስት የሚያከናውነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መንግስት ለአረንጓዴ ልማት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደሆነም ነው የገለፁት።            

የአየር ንብረት ለውጥ ለብዝሀ ህይወትና ለመጪው ትውልድ ስጋት በመሆኑ ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ስለሚገባ ሌሎች አጋር አካላትም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ሁለቱ አገራት በዘርፉ ላይ በጋራ ለመስራት ያደረጉት ስምምነት ከ10 አመት በላይ ማስቆጠሩን አስታውሰዋል፡፡

ይህን ተከትሎ የኖርዌይ የአየር ንብረትና አካባቢ ሚኒስቴር በየካቲት 2016 ዓም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በአየር ንብረት ላይ ያለውን አጋርነት እኤአ እስከ 2030 ለማጠናከር መስማማታቸውን አስታውሰዋል።

በአለም ላይ ብዝሀ ህይወትን ጠብቀው በማቆየት ስኬታማ ከሆኑ 36 አካባቢዎች ሁለቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው ለእነዚህ አካባቢዎች ድጋፍ ይደረጋል ነው ያሉት።  

በቀጣይ የኖርዌይ መንግስት በደን ልማት ላይ የሚያደርገው ድጋፍ እንደሚጠናከር አስታውቀዋል፡፡ 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም