የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ
አዳማ ከተማ ከሲዳማ ቡና ከቀኑ 9 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የሚመራው አዳማ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች 2ቱን ሲያሽንፍ 1 ጊዜ ተሸንፏል። 2 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
በነዚህ 5 ጨዋታዎች 4 ጎሎችን ከመረብ ሲያሳርፍ 3 ግቦች ተቆጥረውበታል። አዳማ ከተማ በ38 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች 2ቱን ሲያሸንፍ 1 ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። 2 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።
በ5ቱ ጨዋታዎች 5 ግቦችን ሲያስቆጥር 4 ግቦች ተቆጥረውበታል። በዘላለም ሽፈራው የሚሰለጥነው ሲዳማ ቡና በ31 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ መለያየቱ የሚታወስ ነው።
በ25ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር ሻሸመኔ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ከምሽቱ 12 ሰዓት ይጫወታሉ።
ሻሸመኔ ከተማ ባለፉት አመስት የሊግ ጨዋታዎች 4 ጊዜ ሽንፈት ሲያስተናግድ 1 ጊዜ አቻ ወጥቷል። ክለቡ በነዚህ 5 ጨዋታዎች 1 ግብ ብቻ ሲያስቆጥር 6 ጎሎችን አስተናግዷል።
በአሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ የሚመራው ሻሸመኔ ከተማ በ13 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች በ2ቱ ድል ሲቀናው 1 ጊዜ ተሸንፏል። 2 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
በ5ቱ ጨዋታዎች 8 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 7 ጎሎችን አስተናግዷል።
በነጻነት ክብሬ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ ቡና በ38 ነጥብ ተመሳሳይ ነጥብ ያለውን አዳማ ከተማን በግብ ክፍያ በልጦ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ መለያየታቸው አይዘነጋም።
በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የ25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መቻል ሃዋሳ ከተማን 3 ለ 2 ሲያሸንፍ ቅዱስ ጊዮርጊስና ሀድያ ሆሳዕና አንድ አቻ ተለያይተዋል።