የክረምቱ ዝናብ ለግብርናና ተጓዳኝ ሥራዎች መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ነው - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
የክረምቱ ዝናብ ለግብርናና ተጓዳኝ ሥራዎች መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ነው - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2016(ኢዜአ)፦ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚዎች በክረምት ወቅት የሚያገኙት መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ለግብርናና ተያያዥ ሥራዎች መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ኢንስቲትዩቱ የበልግ አየር ሁኔታ ትንበያ ግምገማና የመጪው ክረምት የአየር ትንበያ አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዳማ ከተማ ምክክር አካሄዷል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ እንደገለጹት፤ በመጪው የክረምት ወቅት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ የኢትዮጵያ ክፍሎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያኙ የአየር ትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ።
ክረምቱ በምድር መቀነት (ኢኩዌተር) አካባቢ ባለው የፓስፊክ ውቅያኖስ በሚከሰተው ከአማካይ በላይ ቅዝቃዜ (ላኒና) ምክንያት መደበኛና ከመደበኛ በላይ እንዲሁም በተወሰኑ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችል አመልክተዋል።
የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለግብርና፣ ለውሃ ኃብትና ለግጦሽ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
በመካከለኛና የተወሰኑ የኢትዮጵያ ክፍሎች መደበኛ የሆነ ዝናብ ሲያገኙ በተወሰኑ የአገሪቷ አካባቢዎች ከፍተኛ ዝናብና ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ኢኒስቲትዩቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚሰጠው የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ አደጋን ለመቀነስ አስተዋጽኦ ያለው ተግባር መሆኑን ገልጸው ይህ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።