የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - ምክትል አፈ-ጉባዔ ሎሚ በዶ - ኢዜአ አማርኛ
የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - ምክትል አፈ-ጉባዔ ሎሚ በዶ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2016(ኢዜአ)፦ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ሎሚ በዶ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል እየተሰሩ ባሉ ዘርፈ-ብዙ ሥራዎች ዙሪያ የምክር ቤት አመራሮች፣ የባለስልጣኑ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በቢሾፍቱ ውይይት አካሂዷል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ሎሚ በዶ፤ መገናኛ ብዙኃን ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ፣ለህዝብ ተጠቃሚነትና ለልማት መሳካት ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።
በሀገራዊ ለውጡ የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት የማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
አሳሪ የነበሩ ሕጎችን ከመለወጥ አንጻር በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸው፤ በዚህም የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ፣ የፀረ-ሽብር አዋጅ እና የሲቪል ማኅበራትን አዋጅ ለአብነት ጠቁመዋል።
በሀገሪቱ የሚዲያ ነፃነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ዘርፉን በሕግና በእውቀት ለመምራት የተለያዩ ሕጎች ወጥተው ተግባራዊ መደረጋቸውንም ጠቁመዋል።
መገናኛ ብዙኃን የሕዝብንና የሀገርን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ መስራት እንደሚገባቸው የገለጹት ምክትል አፈ ጉባኤዋ፥ ከሀገር ጥቅም በተጻረረ መልኩ የሚሰሩትን በሕጋዊ መንገድ ማረም እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሕዝብንና የሀገርን ደኅንነት ለማረጋገጥ የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አዋጅ ቁጥር 1185/2012 ወጥቶ ተግባራዊ መደረጉንም ጠቁመዋል።
የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት አዋጅን አስመልክቶ በተለያዩ መንገዶች የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የአቅም ግንባታ ዴስክ ኃላፊ ኤደን አማረ፤ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚደረግ የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃን የተመለከተ ሀገራዊ የጥናት ሪፖርት አቅርበዋል።
በጥናቱ መሠረትም የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን በማንሳት፥ ድርጊቱን ለመከላከል የሚመለከታቸው አካላት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩ የተሳተፉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፤ ባለስልጣኑ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል የጀመረውን የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ የሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ዜጎች መረጃዎችን በነፃነት የማግኘት መብት አላቸው ብለዋል፡፡
ሆኖም መረጃዎችን የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ ማሠራጨት እና መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ በበኩላቸው፤ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል የሚረዱ ደንቦችን በፍጥነት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማሕዲ (ዶ/ር) የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን መከላከል የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡
ድርጊቱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሀገር በቀል መተግበሪያዎችን ጭምር እስከማዘጋጀት ሊታሰብበት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው፤ የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን መከላከል ለነገው ትውልድ ሰላም የሰፈነባት ሀገር የማስረከብ አካል ነው ብለዋል፡፡
ባለሥልጣኑ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን ጨምሮ እርምጃ እስከመውሰድ ድረስ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።