ቀጥታ፡

ታዋቂ ግለሰቦች ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም ለቀጣናው ሰላም መረጋገጥ ገንቢ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል - ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2016(ኢዜአ)፦ ታዋቂ ግለሰቦች ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም በቀጣናው ሰላም እንዲሰፍን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንደሚገባቸው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።

ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው የኢጋድ የታዋቂ ግለሰቦች ምክር ቤት ስብስባ ዛሬ ተጠናቋል።

የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ፤ የአገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ታዋቂ ግለሰቦች በማኅበረሰብ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል። 

ግለሰቦቹ በማኅበረሰብ ላይ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም እንዳላቸውም ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ ኢጋድ በሰላም፣ መረጋጋት፣ ቀጣናዊ ትስስር፣ ሕገ-ወጥ ስደትና የድንበር ጉዳዮች ላይ እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎችን እንዲደግፍ መቋቋሙን አመልክተዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት ምክር ቤቱ ቢቋቋምም የሚጠበቅበትን ያህል አልሰራም ያሉት ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በስብሰባው የምክር ቤቱን የመፈጸም አቅም ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከሩን ገልፀዋል።

በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር በርካታ ሥራዎች ቢከናወኑም አሁንም ብዙ ሥራ እንደሚቀርና ከዚህም አንጻር የምክር ቤቱ ሚናና ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ታዋቂ ግለሰቦች ያላቸውን አቅምና በማኅበረሰብ ላይ መፍጠር የሚችሉትን ተጽዕኖ በመጠቀም ሚናቸውን በሚገባ እንዲወጡና ድምፅ ለሌላቸው ድምፅ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

ቀጣናው ግጭትን ጨምሮ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈ ቢሆንም ለችግሮቹ የማይበገር ነው ያሉት ዋና ጸሐፊው በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ የጋራ ጥረት እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።

የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የምክር ቤቱ መቋቋም በግጭትና አለመግባባት ከፍተኛ ጉዳት ላስተናገደው ቀጣናው በጎ ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀዋል።


 

የኢጋድ ራዕይ የሆኑት ሰላም፣ ብልጽግናና ቀጣናዊ ትስስር እውን እንዲሆኑ የታዋቂ ግለሰቦችና የአገር ሽማግሌዎች ጉዳይ ቁልፍ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ምክር ቤቱ ለሚያደርጋቸው ሁሉን አቀፍ ጥረቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።


 

የኢጋድ ታዋቂ ግለሰቦች ምክር ቤት ሊቀመንበር ጆን አያቤ ሴ ምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ጸጥታን ጨምሮ በርካታ ፈተናዎች እንዳሉበት ገልጸው፤ ምክር ቤቱ በቀጣናው ያሉ ችግሮችን ከመፍታት አኳያ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው አንስተዋል።

ምክር ቤቱ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት አበክሮ በመሥራት የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት በሚገባ እንደሚወጣ ገልፀዋል።

የኢጋድ ታዋቂ ግለሰቦች ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ አፍሪካውያን ችግሮቻችንን ለመፍታት ወደ ውጭ መመልከት የለብንም ያለ ሲሆን፤ በራሳችን አቅም ለሚገጥሙን ፈተናዎች መፍትሔ ማበጀት አለብን ሲል ገልጿል።

ለዚህም አገር በቀል የግጭት አፈታት ሥርዓቶቻችንን መጠቀም እንደሚገባና የአገር ሽማግሌዎችም ከዚህ አኳያ ወሳኙን ሚና እንደሚወጡ ተናግሯል።

ምክር ቤቱ ዛሬ ስብሰባውን በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ ያደረገ ሲሆን፤ ትናንት የቴክኒክ ስብሰባውን አካሂዷል።

ባለፈው ዓመት በተቋቋመው የኢጋድ የታዋቂ ግለሰቦች ምክር ቤት ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያና ዩጋንዳ የምክር ቤቱ አባላት ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም