አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ከማስቀጠል ጎን ለጎን ለአገር ውስጥ መዳረሻዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው - ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው - ኢዜአ አማርኛ
አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ከማስቀጠል ጎን ለጎን ለአገር ውስጥ መዳረሻዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው - ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ከማስቀጠል ጎን ለጎን ለአገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርት ትስስርና መዳረሻዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በ50 ሚሊየን ዶላር ያስገነባውን የአገር ውስጥ የመንገደኞች ተርሚናል ማስፋፊያና እድሳት ፕሮጀክት ዛሬ አስመርቋል።
በማስመረቂያው መርሃ-ግብር የቱሪዝም ሚኒስትር ናሲሴ ጫሊ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያዴቻ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሐሰንና ሌሎችም የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ጊዜ፤ የአፍሪካ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ላይ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማስቀጠል ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የአገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርትን ለማስፋፋት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የቦሌ አየር መንገድ የአገር ውስጥ የመንገደኞች ተርሚናል ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ መሆኑን በማንሳት፤ ዛሬ ላይ የማስፋፊያና እድሳት ፕሮጀክት ግንባታ መደረጉ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልፀዋል።
ይህም በአገሪቷ እየጨመረ የመጣውን የመንገደኞች ቁጥርና የቱሪስት ፍሰት ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ነው ያሉት።
አየር መንገዱ አሁን ላይ 22 ያህል የአገር ውስጥ መዳረሻዎች ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም በቀን በአማካይ ከ200 በላይ የአገር ውስጥ በረራዎችን በመላው አገሪቷ እንደሚያከናውን ገልፀዋል።
ይህ ቁጥር በጥቂት ዓመታት ውስጥ እጥፍ እንደሚሆን ያነሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ''ይህንኑ የደንበኞች ቁጥር በሚመጥን መልኩ በመላው አገሪቷ የአውሮፕላን ማረፊያዎችና ተርሚናል ግንባታዎችን በማፋጠን ላይ እንገኛለን'' ብለዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚ እድገት ልዩ ትኩረት ከሰጠችባቸው ዋንኛ ዘርፎች አንዱ ቱሪዝም መሆኑን በማንሳት በዚህ ረገድ አየር መንገዱ ልዩ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።
በመሆኑም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ብሎም የአገር ውስጥ ቱሪዝምን በአየር ትራንስፖርት በማስተሳሰር የሚጠበቀውን ውጤት ለማስመዝገብ ቁልፍ ሚና የሚጫወት ይሆናል ነው ያሉት።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሐሰን፤ ኢትዮጵያ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉ እየሰጠች ያለውን ትኩረት ማሳያ ከሆኑት መካከል አየር መንገዱ እንደ ተምሳሌት የሚቆጠር ነው ብለዋል።
ይህ የሀገር ውስጥ የመንገደኞች ተርሚናል ማስፋፊያና እድሳት ፕሮጀክት ግንባታ "ሲሲሲሲ" በተሰኘው የቻይና ኩባንያ የተሰራ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱን በማማከር ደግሞ "ዳር" ኩባንያ የተሰኘ ድርጅት መሳተፉን ተገልጿል።