ቀጥታ፡

የሳይበር ደኅንነት ለማረጋገጥና ተቋማት በዘርፉ ያላቸውን አቅም ለማጠናከር የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2016 (ኢዜአ) ፡- የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የሳይበር ደኅንነት ለማረጋገጥና ተቋማትን በዘርፉ ያላቸውን አቅም ለማጠናከር የሚያከናውነው ተግባራት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ። 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደርን ጎብኝተዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ፤ የሳይበር ታለንት ልማት ማዕከልን፣ የአስተዳደሩን የዲጂታል ኤግዚቢሽን፣ ይፋዊ ቁልፍ መሠረተ-ልማት ጨምሮ የተቋሙን የተለያዩ የሥራ ክፍሎች አስጎብኝተዋቸዋል። 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱን የሳይበር ደኅንነት ለማረጋገጥ በአስተዳደሩ እየተሰሩ ያሉ ዋና ዋና ሥራዎችን ተመልክተዋል። 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ጊዜ፤ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች አበረታችና ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

ተቋሙ ከለውጥ በኋላ ሪፎርም ካካሄዱ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑን አንስተው፤ ሪፎርሙን በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በራስ አቅም የተገነቡ ሲስተሞችን ተግባራዊ በማድረግ የሳይበር ደኅንነት ለማረጋገጥ የተሰሩ ሥራዎች መመልከታቸውንና ሊበረታቱ የሚገባ መሆናቸውንም ነው ያነሱት። 


 

ከዚህም በተጨማሪ ተቋሙ የሚሰራቸው ሥራዎች ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 እውን እንዲሆን የሚያግዝና በተለይም ችግር ፈቺ የሆኑ ሥርዓቶች በመገንባት ተቋማትን እየደገፈ መሆኑን ገልፀዋል።

ከዚህ አንጻር፤ ተቋሙ በተለይም ከገቢዎች ሚኒስቴርና ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር ያከናወናቸው ተግባራት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

ተቋሙ እንደ አገር ከሚያከናውነው የሳይበር ደኅንነት የማረጋገጥ ሥራ በተጨማሪ ቁልፍ የሆኑ የፋይናንስ ተቋማት የራሳቸውን የሳይበር ደኅንነት እንዲገነቡ እያደረገ ያለው እገዛም የሚበረታታ መሆኑን  አንስተዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን የሳይበር ሰራዊት እንዲገነባ የሚያከናውናቸው ተግባራት የሚበረታቱ መሆኑን ተናግረዋል። 

የመንግሥት ደኅንነቱ የተጠበቀ ግንኙነት ሥርዓት ለመገንባት የተጀመሩ ሥራዎች እንዲሁም የሳይበር ጥቃትን መመከት የሚያስችሉ ዘመኑ የደረሰባቸውን መሠረተ-ልማቶች መመልከታቸውን ጠቅሰዋል። 

ይህንን ተከትሎ ተቋሙ በሰው ኃይል አስተዳደሩ እንዲሁም በአሠራር ሥርዓቱ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በጉብኝታቸው የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የመሥራትና የማድረግ አቅሙ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።


 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ፤ አስተዳደሩ አገራዊ የሳይበር ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህን ሥራዎች ተዘዋውረው መመልከታቸውን በመግለፅ የሥራ አቅጣጫ መስጠታቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም አስተዳደሩ እያደገ የመጣውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና ዲጂታል ኢኮኖሚ ተከትሎ የሚከሰተውን የሳይበር ተጋላጭነት መመከት የሚያስችል አቅም መገንባት እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

እንዲሁም ቁልፉ በሆኑ መሠረተ-ልማቶች ላይ የሚደረግ ጥበቃና ክትትል ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቅጣጫ ማስቀመጣቸውንም አክለዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም