ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ25ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሀድያ ሆሳዕና ከቀኑ በ 9 ሰዓት፤ ሐዋሳ ከተማ ከመቻል ከቀኑ 12 ሰዓት በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በፕሪሚየርሊጉ ባለፉት 5 ጨዋታዎች፤ 3 ጊዜ አሸንፎ ሁለት አቻ በመውጣት በአምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በእነዚህ 5 ጨዋታዎች 7 ጎሎችን ሲያስቆጥር 6 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የሚመራው ሀድያ ሆሳዕና ደግሞ ባለፉት 5 ጨዋታዎች 2 ጊዜ አሸንፎ፣ ሁለት ተሸንፎና አንድ ጊዜ አቻ በመውጣት በስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በእነዚህ 5 ጨዋታዎች 5 ጎል ሲያስቆጥር፤ 5 ጎሎች ደግሞ ተቆጥረውበታል።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 2 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

አጠቃላይ እስካሁን ዘጠኝ ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 4 ጊዜ ሲያሸነፍ፤ ሀዲያ ሆሳዕና 2 ጊዜ በማሸነፍ 3 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።

ሌላኛው የ25ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ሐዋሳ ከተማ እና መቻልን ከምሽቱ 12 ሰዓት ያገናኛል።

ሐዋሳ ከተማ ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች ሁለቱን በማሸነፍ፤ ሁለቱን በመሸነፍና አንድ አቻ በመውጣት በ10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።  

በእነዚህ 5 ጨዋተዎች 8 ጎሎች ሲያስቆጥር፤ 7 ጎሎች ደግሞ ተቆጥረውበታል።  

መቻል በበኩሉ ካለፉት 5 ጨዋታዎች ሁለት በማሸነፍ፤ ሁለት አቻ በመውጣት፤ አንድ ጨዋታ ደግሞ ተሸንፏል።  

በእነዚህ 5 ጨዋታዎች 5 ጎሎች ሲያስቆጥር፤ 4 ጎሎች ተቆጥረውበት በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሁለቱ ቡድኖች 33 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን፤ ሐዋሳ ከተማ 14 ጊዜ ሲያሸንፍ መቻል ደግሞ 9 ጨዋታዎች አሸንፏል፤10 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

ትናንት በተደረጉ የ25ኛ ሳምንት የሁለተኛ  ቀን ጨዋታዎች፤ ኢትዮጵያ መድን  ድሬደዋ ከተማን 5 ለ 0፤ ባህርዳር ከተማ ሀምበሪቾን 2 ለ 0 አሸንፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም