የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ፌስቲቫልና አውደ ርዕይ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ፌስቲቫልና አውደ ርዕይ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው
አርባምንጭ፤ ግንቦት 10/2016 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዓላማው የክልሉን እምቅ የባህልና የቱሪዝም ሀብቶችን ማስተዋወቅ ያደረገ የባህልና ቱሪዝም ፌስቲቫልና አውደ ርዕይ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ፌስቲቫሉና አውደ ርዕዩ "የባህልና ቱሪዝም ሃብቶቻችን ለመቻቻል፣ ለሰላምና ለሁለንተናዊ ብልፅግና" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ መሆኑም ተገልጿል።
የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች የክልሉን የባህልና የቱሪዝም ሃብቶች አውደ ርዕይን በይፋ መርቀው ከፍተዋል።
በመድረኩ ላይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በኩል የክልሉን የባህልና የቱሪዝም አቅም የሚያሳይ ሰነድ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበትም ተገልጿል።
የተለያዩ ቱባ ባህላዊ ጭፈራዎች በባህላዊ አልባሳት ደምቀው ለታዳሚው በመቅረብ ላይ ይገኛሉ።
በፕሮግራሙ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ፣ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልማሃዲ ተገኝተዋል።
እንዲሁም የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ወይዘሪት ፍሬህይወት ዱባለ፣ የክልሉ አፈ-ጉባኤ ፀሀይ ወራሳ፣ የብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አዳማ ትንጳዬን ጨምሮ የክልልና የዞን ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችም ታድመዋል።
በተጨማሪም የተለያዩ የባህል አምባሳደሮች፣ የባህላዊ ሙዚቃ ተጫዋቾች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ብዙሃን መገናኛዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም ተገኝተዋል።