የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገር ውስጥ የመንገደኞች ተርሚናል ማስፋፊያ ፕሮጀክት አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገር ውስጥ የመንገደኞች ተርሚናል ማስፋፊያ ፕሮጀክት አስመረቀ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በ50 ሚሊየን ዶላር ሲያሰራ የቆየውን የአገር ውስጥ የመንገደኞች ተርሚናል ማስፋፊያና እድሳት ፕሮጀክት አስመረቀ።
በማስመረቂያው መርሃ-ግብር ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር ናሲሴ ጫሊ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያዴቻ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሐሰን እና ሌሎችም የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀጥል እየተሰራ ነው ብለዋል።
የቦሌ አየር መንገድ የሀገር ውስጥ የመንገደኞች ተርሚናል ለበርካታ አመታት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ መሆኑን አንስተዋል።
ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የተደረገው ይህ የማስፋፊያ ፕሮጀክትም የሀገር ውስጥ መንገደኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንና የሀገር ውስጥ የቱሪዝም መስህብ እየጨመረ በመምጣቱ ያንን የሚመጥን እንዲሆን ተደርጎ መሰራቱን ገልጸዋል ።