ለሕዝብ አብሮነት ሳንካ እየሆኑ የመጡ የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃዎች በጋራ ልንከላከላቸው ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ለሕዝብ አብሮነት ሳንካ እየሆኑ የመጡ የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃዎች በጋራ ልንከላከላቸው ይገባል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2016 (ኢዜአ)፦ ለሕዝብ አብሮነትና ለሀገር ሰላም ፈተና እየሆኑ የመጡ የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃዎችን በጋራ ልንከላከላቸው ይገባል ሲሉ ምክትል አፈ- ጉባዔ ሎሚ በዶ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል በተቋሙ እየተሰሩ ባሉ ዘርፈ-ብዙ ሥራዎች ዙሪያ በቢሾፍቱ ውይይት እየተካሄደ ነው።
በዚሁ መድረክ ላይ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ- ጉባዔ ሎሚ በዶ፤ መገናኛ ብዙኃን ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ ስኬት ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።
የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ልማትን ለማፋጠን እንዲሁ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።
በሀገሪቱ የሚዲያ ነፃነትን ለማረጋገጥ ዘርፈ-ብዙ ሥራዎች መከናወናቸውን የጠቆሙት ምክትል አፈ- ጉባዔዋ፤ ዘርፉን በሕግና በእውቀት ለመምራትም የተለያዩ ሕጎች ወጥተው ተግባራዊ መደረጋቸውንም ጠቁመዋል።
ሀገራዊ ለውጡ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ከማስፋት ባሻገር የመገናኛ ብዙኃን ሪፎርሞች መሠራታቸውን ተናግረዋል።
አሳሪ የነበሩ ሕጎችን ከመለወጥ አንጻር በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸው፤ በዚህም የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ፣ የፀረ-ሽብር አዋጅ እና የሲቪል ማኅበራትን አዋጅ ለአብነት ጠቁመዋል።
የሚዲያ ተደራሽነትን ከማስፋት አንጻርም በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመው፤ መገናኛ ብዙኃን የሕዝብንና የሀገርን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ መጠቀም እንደሚገባቸውም ገልፀዋል።
በዚህ መልኩ የማይሄዱትን ሕጋዊ በሆነ መንገድ ማረም እንደሚገባም ነው የጠቆሙት።
የሕዝብንና የሀገርን ደኅንነት ለማረጋገጥ የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አዋጅ ቁጥር 1185/2012 ወጥቶ ተግባራዊ መደረጉንም ጠቁመዋል።
በዚህም የጥላቻ ንግግርን በማንኛውም የመረጃ ማሠራጫ ጣቢያ ማሠራጨት የተከለከለ መሆኑን ይገልጻል ብለዋል።
የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት አዋጅን አስመልክቶ በተለያዩ መንገዶች የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ ጠቁመው፤ አዋጁን የሚተላለፉ አካላት በሕግ ማዕቀፉ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ተቋሙ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ተናግረዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈላጊውን ሁሉ ክትትል እና ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው፤ የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ ይገኛል ብለዋል።
ባለሥልጣኑ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል ከግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ባሻገር ሌሎችንም ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
መመድረኩ በማኅበራዊ ሚዲያ ጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ሀገራዊ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እየተካሄደበት ይገኛል።
በመድረኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ሎሚ በዶን ጨምሮ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሃመድ እድሪስ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራሮች እና አባላት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የሥራ እንቅስቃሴን መጎብኘታቸው ይታወሳል።