ቀጥታ፡

የፓሪሱ ኦሎምፒክን በወርቅ በታጀበ ድል ለማሳለፍ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ገለጸ

ሀዋሳ ፤ ግንቦት 10 / 2016 (ኢዜአ) ፡-መጪው የፓሪስ ኦሎምፒክን  በወርቅ የታጀበ ድል በማስመዝገብ  ለማሳለፍ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን  የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ገለጸ።

በሀዋሳ ከተማ የኦሎምፒክ ችቦ ቅብብሎሽ ንቅናቄን አስመልክቶ የፓናል ውይይት ተካሂዷል ።

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ  ዋና ፀሐፊ አቶ ዳዊት አስፋው በወቅቱ እንደተናገሩት ፤ የፓሪስ  ኦሎምፒክ ችቦ ቅብብሎሽ ንቅናቄ  በሲዳማ ክልል ሲካሄድ ሰባተኛው ነው ።

በዚህም ኮሚቴው የኦሎምፒክ ፅንሰ ሀሳቦችን በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ይበልጥ ለማፅናት አትኩሮ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

በተለይ አብሮነት አንድነትና እርስ በእርስ መከባበር እንዲሁም ፍቅር ከኦሎምፒክ ጽንሰ ሀሳቦች መካከል እንደሚጠቀሱ አንሰተዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቶች በወርቅ የታጀበ የድል ታሪክ ያላቸው መሆናቸውን ያወሱት  አቶ ዳዊት፤  በመጪው ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ በሚካሄደው በፓሪሱ ኦሎምፒክም እንደዚሁ ውጤት በማስመዝገብ ለማሳለፍ አስፈላጊው  ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁን ወቅት በፓሪስ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ተለይተው ወደ ሆቴል ገብተው እየተሰናዱ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

የሲዳማ ክልል ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ በበኩላቸው፤  የኦሎምፒክ ችቦ ቅብብሎሽ ንቅናቄ  አገራዊ አንድነትን፣ ፅናትን፣ ስፖርታዊ ጨዋነትን የሚያመለክት እንደሆነ ተናግረዋል።

አንድነትንና አብሮነትን እያጠናከርን የአሸናፊነትና የታላቅነትን ተስፋ በውስጣችን ሰንቀን ለኢትዮጵያ ከፍታ እንድንተጋ የሚያደርገን ነው ብለዋል ።

የኦሎምፒክ ችቦ ቅብብሎሹ ንቅናቄ  በክልሉ የሚፈጥረውን መነቃቃትና የህብረተሰቡን እምቅ አቅም በመጠቀም የስፖርቱን ህዝባዊ መሠረት ለማስፋት በትኩረት እንደሚሰሩም ገልጸዋል ።

ክልሉ በዓለም አትሌቲክስ መድረክ ኢትዮጵያን ያስጠሩ በርካታ አትሌቶችን ያፈራ ነው ያሉት ደግሞ የሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍሬው አሬራ ናቸው።  

ለአብነት የማራቶን ባለድሉ አትሌት መቶ አለቃ በላይነህ ዲንሳሞ የአለም ክብረ ወሰን ባለቤትም ጭምር እንደነበር አስታውሰዋል።

ክልሉ አሁንም ተተኪ አትሌቶችን እያፈራ መሆኑን ጠቁመው ፤ ተሳትፎና አስተዋጽኦውን  ይበልጥ ለማጠናከር እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።

በፓናል ውይይቱ ወቅት የተገኘው አትሌት በላይነህ ዲንሳሞ በተለያዩ የዓለም መድረኮች በአትሌቲክስ ኢትዮጵያን መወከል እንደቻለ ጠቅሶ ፤ በማራቶን ለ10 ዓመታት የክብረ ወሰን ባለቤት ሆኖ መቆየቱን አውስቷል ።

ለስኬታማነቱ የጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላን ፅናትና አሸናፊነት አርአያ ማድረጉ በእጅጉ እንደረዳው ተናግሯል ።

በፓናል ውይይት ላይ የኦሎምፒክ ኮሚቴ አመራር አባላት፣  የሲዳማና ሌሎች ክልሎች የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎችና የስፖርት ቤተሰቦች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም