ቀጥታ፡

ለድንበር ተሻጋሪ የከባድ የጭነትና አገር አቋራጭ  የህዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ዕውቅና ተሰጠ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 9/2016(ኢዜአ)፦ በሙያቸው የላቀ አበርክቶ ላደረጉና ለረጅም አመት ላገለገሉ ድንበር ተሻጋሪ የከባድ የጭነትና አገር አቋራጭ  የህዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች  ዕውቅና ተሰጠ።

የዕውቅና መርሐ ግብሩን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከተለያዩ የዘርፉ አጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።

በዝግጁቱ ላይም የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትር  አለሙ ስሜ( ዶ/ር)ን ጨምሮ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ አሽከርካሪዎች፣ የዘርፉ ማህበራትና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።


 

በመርሐ ግብሩ ላይ ከባድ የጭነትና አገር አቋራጭ አሽከርካሪዎች ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የማይተካ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

የሠዎችና የሸቀጦች ዝውውር የተሣለጠ እንዲሆን ያልተመቻቸ መሠረተ ልማት ሳይበገራቸው የበኩላቸውን ኃላፊነት እየተወጡ በመሆኑ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

በመርሐ ግብሩም ለረጅም ዓመታት ሀገር በማገልገል ለሁለንተናዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ለሚገኙ  አሽከርካሪዎች  እውቅና መሰጠቱን ገልጸዋል።

እውቅናው የከባድ መኪና አሽከርካሪዎችን የስራ ተነሳሽነትን ለማዳበር፣ መልካም ስነ- ምግባር ያለውና ሃላፊነት የሚሰማው  ብቁ ባለሙያ ለመፍጠር  የተካሄደ መርሐ ግብር ነው።

ዕውቅና የተሠጣቸውም የሙያውን ስነ-ምግባር በመጠበቅ ከትራፊክ አደጋ የጸዳ አገልግሎት ለሰጡ ባለሙያዎች መሆኑን ገልጸው፤  በቀጣይም የትራፊክ አደጋንም ሁሉም በጋራ እንዲከላከል ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎችና ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ  ደጀኔ ሙጬ አሽከርካሪነት ሀገርና ወገን የሚጠቅም አገልግሎት የሚሰጡበት የተከበረ ሙያ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ ጥንቁቅና ምስጉን አሽከርካሪዎች ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው ለምስጉን ባለሙያዎች የሚሰጡ እውቅናዎች ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የተሳተፉ አሽከርካሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የዕውቅና መርሐ ግብሩ በመካሄዱ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም