የፀሐይ ኃይልን በመጠቀም የከርሰ ምድር ውሃን ለመስኖ አገልግሎት ለማዋል በስፋት እየተሰራ ነው- ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የፀሐይ ኃይልን በመጠቀም የከርሰ ምድር ውሃን ለመስኖ አገልግሎት ለማዋል በስፋት እየተሰራ ነው- ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 9/2016(ኢዜአ)፦ የፀሐይ ኃይልን በመጠቀም የከርሰ ምድር ውሃን ለመስኖ አገልግሎት ለማዋል በስፋት እየተሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሚኒስቴሩ በፀሃይ ሃይል የሚሰሩ የውሃ መሳቢያ ፓምፖች ለመስኖ ልማት ያላቸውን ጠቀሜታ ለአርሶ አደሮች ለማስተዋወቅ ያለመ የፓናል ውይይት አካሒዷል፡፡
በፓናል ውይይቱ አርሶ አደሮች፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ የፋይናንስ ተቋማትና የሶላር ኢነርጂ ምርት አቅራቢዎች ተሳትፈዋል፡፡
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር ዋና ስራ አስፈጻሚ ብርሃኑ ወልዱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤እኤአ በ2030 የኢነርጂ ሃይልን ለዜጎች ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡
በዚህም የሃይል አቅርቦቱ 65 በመቶው ከዋናው ግሪድ ፤ ቀሪው 35 በመቶ ደግሞ ከአማራጭ የሃይል ምንጮች የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከአጠቃላይ የአገሪቱ ህዝብ 49 በመቶ የሚሆነው የትኛውንም አይነት ሃይል እንደማያገኝ በመጥቀስ ፍላጎቱን ለማሟላት ከውሃ ከሚገኘው በተጨማሪ አማራጭ የኃይል ምንጮችን መጠቀም የግድ ነው ብለዋል፡፡
ይህን ተከትሎ በመላ አገሪቱ ከ300 በላይ አነስተኛ የሃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እየተገነቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሃይል አማራጮቹ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች ተደራሽ በማድረግ ምርትና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ የጎላ ሚና እንደሚኖራቸው አስረድተዋል፡፡
ካሉት አማራጮች በተለይም የፀሐይ ኃይልን በመጠቀም የከርሰ ምድር ውሃን ለመስኖ አገልግሎት ለማዋል ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ የልማት ድርጀት የኢነርጂ ዘርፍ ሃላፊ ህይወቴ ተሾመ በበኩላቸው፣ ድርጀቱ በተለይ በፀሃይ ሃይል የሚሰሩ ቴከኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
ድርጅቱ በተለያዩ ክልሎች የፀሃይ ሃይል ለአርሶ አደሩ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሶላር ሃይል ልማት ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ተዋበች ወርቄ ፤ በተለይ በገጠር አካባቢ ያለውን የሃይል እጥረት ለመቅረፍ የፀሃይ ሃይል ትልቅ አማራጭ ነው ብለዋል፡፡
ማህበሩ አርሶ አደሮች የፋይናንስ ችግር እንዳይገጥማቸው ከአበዳሪ ተቋማት ጋር የማገናኘት ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
አርሶ አደር መሰረት ጌታቸው እና ኢብራሂም ረዲ፤ ከዚህ ቀደም በነዳጅ የሚሰሩ የውሃ ፓምፖች ይጠቀሙ እንደነበርና ይህም ለከፍተኛ ወጪ ሲዳርጋቸው መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
የፀሃይ ሃይል መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ምርታማነታቸው መጨመሩንና ወጪያቸው በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ተናግረዋል፡፡