ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የማይወጡ የመገናኛ ብዙኃንን ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የማይወጡ የመገናኛ ብዙኃንን ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 9/2016(ኢዜአ)፦የዜጎችን የአብሮነት እሴት የሚሸረሽሩና ሐሰተኛ መረጃን የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙኃንን ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ ሊጠናከር እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶን ጨምሮ የምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና ምክትል ሰብሳቢዎች የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንን የሥራ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።
ባለሥልጣኑ የመገናኛ ብዙኃን የሚከታተልበትና የሚቆጣጠርበት እንዲሁም ዜጎች ጥቆማና አስተያየት የሚሰጡበትን በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ተጎብኝቷል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፣ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታና ጥያቄ ይነሳባቸው ከነበሩ አዋጆች መካከል የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ አንዱ ነው።
ምክር ቤቱ ከአገራዊ ለውጡ በኋላ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን ጨምሮ ሌሎች አሳሪ ሕጎችን በማሻሻል ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል።
መገናኛ ብዙኃንም የተሰጣቸውን ነጻነት በአግባቡ በመጠቀም ኃላፊነታቸውን መወጣትና ለማኅበረሰብ ተገቢና ጠቃሚ መረጃዎችን ማስተላለፍ እንደሚገባቸውም ነው ያሳሰቡት።
ባለሥልጣኑም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በማይወጡ፤ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ እንዲሁም ሐሰተኛ መረጃዎችን በሚያሰራጩ የመገናኛ ብዙኃንን ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የመገናኛ ብዙኃንን አቅም በመገንባት ለኅብረተሰቡ ወቅታዊ መረጃ እንዲደርስ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን መከተሉን አድንቀዋል።
አያይዘውም የመገናኛ ብዙኃን የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ለማድረግ ተቋማቱን በገለልተኝነት የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራ በምን መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ማብራሪያ ጠይቀዋል።
የተጀመሩት የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎችም ይበልጥ ተጠናከረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሃመድ እድሪስ፣ ባለሥልጣኑ ሁሉንም የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በገለልተኝነት ለማገልገል አሰራር ዘርግቶ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
ገለልተኝነት የሕዝብና የአገርን ጥቅም ማስቀደም መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ የትኛውም አይነት መገናኛ ብዙኃን የሚዲያ ሕጉን አክብሮ ካልሰራ ከተጠያቂነት እንደማያመልጥ አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል ባለሥልጣኑ አሰራሩን ለማዘመን የሚያስችለውን ''የኢትዮጵያ የዲጂታል ሚዲያ አስተዳደር ሥርዓትን በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።
ቴክኖሎጂው ኅብረተሰቡ ጥቆማዎችንና ቅሬታዎችን በቀላሉ ማቅረብ የሚችሉበትና ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ቀጥታ ግንኙነት መፍጠር የሚቻልበት መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።