በግጭትና በተፈጥሮ አደጋዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት የስራና ክህሎት ሚኒስቴር የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በግጭትና በተፈጥሮ አደጋዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት የስራና ክህሎት ሚኒስቴር የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 9/2016(ኢዜአ)፦ በግጭትና በተፈጥሮ አደጋዎች የተፈናቀሉ ዜጎች በዘላቂነት ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት የስራና ክህሎት ሚኒስቴር የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ገለጸ፡፡
በአውሮፓ ህብረት ድጋፍ በአማራ፣ በትግራይ፣ በአፋር እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በግጭትና በተፈጥሮ አደጋዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት መደገፍ የሚያስችል የ43ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ የሚከናወኑ ተግባራት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም በግጭትና በተፈጥሮ አደጋዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም እና በዘላቂነት ለመደገፍ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማገዝ ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን እና ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት ይሰራል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ፕሮጀክቱ በዋናነት የዜጎችን ህይወት በዘላቂነት በሚያሻሽሉ በክህሎት ስልጠና፣ በግጭቱ ለተጎዱ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ብድር አቅርቦት፣ በውሃ፣ በንፅህና አጠባበቅ አገልግሎቶች፣ በማህበራዊ ትስስር እና በመሳሰሉት ተግባራት ላይ አትኩሮ ይፈጸማል ተብሏል፡፡
ይህ ፕሮጀክት በዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት(አይኦኤም) መሪነት ከኢጣሊያ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (AICS)፣ ከጀርመን አለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ(ጂአይዜድ)፣ ከዴንማርክ ቀይ መስቀል ከሚደገፈው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር በመተባበር እንደሚተገበርም ተጠቁሟል፡፡