የሚድዋይፎችን ቁጥር ለመጨመር ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሚድዋይፎችን ቁጥር ለመጨመር ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 9/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የሚድዋይፎችን ቁጥር ለመጨመር ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
ዓለም አቀፍ የሚድዋይፎች ቀን ዛሬ በአዲስ አበባ ተከብሯል።
በመርኃ ግብሩ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ዓለም አቀፍ አጋር አካላት ታድመዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ የማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፣ ሚድዋይፎች ለጤናው ዘርፍ አገልግሎት ወሳኝ ናቸው።
ይህንንም ከግምት በማስገባት መንግሥት በኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ቁጥር ለመጨመር እንዲሁም በዘርፉ የተሰማሩ የህክምና ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በጤና ሚኒስቴር የጤና ዘርፍ የሰው ኃብት ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አሰግድ ሳሙኤል በበኩላቸው፣ የሚድዋይፎች ሚና ለእናቶችና ሕጻናት ጤንነት መጠበቅ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲያም ሆኖ በኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ቁጥር ከሕዝቡ ጋር ያለውን ስብጥር አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰው የሚድዋይፎችን ቁጥር ለመጨመር ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በትበብር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ሰለሞን ኃይለመስቀል በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ሚድዋይፎች ቁጥር እየተሻሻለ ቢሆንም በዘርፉ ተጨማሪ የሠለጠነ የሰው ኃይል ለማስፋት ብዙ መሥራት ይጠይቃል ብለዋል።