ቀጥታ፡

በሀገሪቱ ቅርሶች በተደራጀ አግባብ የሚቀመጡበት ሙዚየሞች የማስፋፋትና የማዘመን ስራ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 9/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ቅርሶች በተደራጀ አግባብ የሚቀመጡባቸውን ሙዚየሞች የማስፋፋትና  የማዘመን ስራ እየተሰራ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዓለም አቀፍ የሙዚየም ቀን "ሙዚየሞች ለትምህርትና ለምርምር " በሚል መሪ ቃል በፓናል ውይይት አክብሯል። 


 

በዕለቱም ዓለም አቀፍ የሙዚየም ቀን በአል አከባበር ፣ታሪካዊ ዳራና ፋይዳዎችን የሚዳስስ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል። 

የቱሪዝም  ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ  ሀገሪቱ ከቱሪዝም ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን  ገቢ ለማጎልበት ያሉንን ቅርሶች በተደራጀ አግባቡ የሚቀመጡባቸውን ሙዚየሞች ማስፋፋትና ያሉትን ማዘመን ይኖርብናል ብለዋል።

ባልተደራጀ መልኩ ተበታትነው የሚገኙ ቅርሶችን ደህንነት ለማስጠበቅ አቅም የሚፈጥር  አዲስ ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል።

ሙዚየሙ ሰዎች ሀገሪቱ  ያላትን ታሪክ፣ ባህልና ሌሎች ቅርሶችን በአንድ ቦታ የሚያዩበት እና ትምህርት የሚቀስሙበት እድልን በቀላሉ የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም ጠንካራ ሙዚየም በገነባን ቁጥር ጥናት ምርምር ለሚያደርጉ አካላቶች የሚፈልጉትን መረጃ በቀላል እንዲያገኙ እንደሚያደርግም አክለዋል።

እንደ ሀገር ያሉን በርካታ  ቅርሶችን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር በተለያዩ አካባቢዎችና ግለሰቦች እጅ ተበታትነው የሚገኙ ቅርሶችን በአንድ ማሰባሰብ የሚችል ሙዚየም መገንባት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

መንግስትም ቅርሶችን ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ እንዲቀመጡ ለማድረግ አዳዲስ ሙዚየሞችን የመገንባት እና ያሉትንም የማሻሻል ስራ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ይህም እውን እንዲሆን ሙዚየሙን መገንባት የሚቻልበትን ምቹ ቦታዎችን ለመምረጥ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም በሀገሪቱ ሙዚየምን የማስፋፋት ስራ በመንግስት ብቻ ሊሸፍን እንደማይችል ገልጸው፤ መሰማራት የሚፈልጉ ግለሰቦችና ተቋማት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው ባለስልጣኑ በዛሬው እለት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ47ኛ በኢትዮጵያ ለ22ኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ የሙዚየም ቀንን "ሙዚየሞች ለትምህርት እና ለምርምር " በሚል መሪ ቃል አክብሯል ብለዋል።


 

በዓሉም  ኢትዮጵያውያን ስለ ሀገራቸው የቱሪዝም ሀብት በተገቢው እንዲረዱ ብሎም የውጭ ሀገር ዜጎች ሀገሪቱ  ያላትን ታሪክ ለማስተዋወቅ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገሪቱ  ያሏትን ሙዚየሞች ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

በዘርፉ በርካታ ለውጦች ቢስተዋሉም እንደ ሀገር ያሉንን የቱሪዝም ሀብቶች በአንድ ብሄራዊ ሙዚየም ማስቀመጥ ብቻ በቂ አለመሆኑን ገልጸው፤ ይህንንም ክፍተት ለመሙላት የሚሰሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም