ቀጥታ፡

የመከላከያ ሠራዊት በህገ መንግሥቱ የተሰጠውን ተልዕኮ በላቀ ብቃት እየተወጣ ነው - ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ

ሀዋሳ፤ ግንቦት 9/2016(ኢዜአ)፡- የሀገር መከላከያ ሠራዊት በህገ መንግሥቱ የተሰጠውን ተልዕኮ በላቀ ብቃት እየተወጣ ነው ሲሉ  የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ አስታወቁ።

ብላቴ የሚገኘው የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ያሰለጠናቸውን 42ኛ ዙር የኢትዮጵያ ኮርስ መሰረታዊ ኮማንዶ ዛሬ አስመርቋል።

የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን የማጠናከሩ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል።


 

የሀገር መከላከያ ሠራዊት በህገ መንግሥቱ የተሰጠውን ተልዕኮ በላቀ ብቃት እየተወጣ መሆኑን ያስታወቁት  ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ፤ በተለይ ከየትኛውም አቅጣጫ የሚቃጣን አደጋ ለመቀልበስና የሀገሪቱን ሉአላዊነት ለማስከበር ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

ሠራዊቱ በእሳት የተፈተነ ጀግና መሆኑን አመልክተው፤ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ከመቼውም ጊዜ በላይ ዘመኑን የዋጀ ሠራዊት ለማፍራት ጠንካራ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተለይ የሥልጠና ካሪኩልም በማሻሻል በጥናትና ምርምር የተደገፈ ስልጠና እየሰጠ ነው ብለዋል።

በዚህም ማዕከሉ የዛሬ ምረቃ ኮርስም እስካሁን ከነበረው በእጅጉ የተለየ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የዛሬ ተመራቂዎች የተሰጣቸው ኃላፊነት የተለየ መሆኑን ተገንዝበው የገቡትን ቃል ኪዳን በአግባቡ እንዲፈጽሙ አሳስበዋል።

የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ በበኩላቸው፤ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ብቃት ያለውን ኃይል ለማፍራት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ ብቃት ያለውን ሠራዊት በመገንባት ለሀገራዊ ሠላምና ደህንነት መረጋገጥ የማይተካ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ተመራቂዎቹ በቆይታቸው በኮማንዶ ቴክኒክ የበቁና በወታደራዊ ሳይንስ ጥበብ የተካኑ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ብላቴ የሚገኘው የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል አዛዥ ኮረኔል ቦጃ አጋ ናቸው። 

ማዕከሉ የማሰልጠን አቅም ባልተቋረጠ ሂደት ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የፌዴራልና የክልል የፀጥታ ሃይሎችን ከመደገፍ አኳያም ዛሬ ከተመረቁት ውስጥ የፌዴራል ፖሊስ አባላት እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

የአሁኑ ዙር ተመራቂዎች ማዕከሉ በሙሉ አቅሙ ወደ ፕሮፌሽናል ሠራዊት ግንባታ በገባበት ሂደት ካለፈው አውደ ውጊያ ልምድና ተሞክሮ በመውሰድ የሰለጠኑ መሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም